የኢትዮጵ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአራት ዓመት ከስድስት ወራት የስራ ቆይታ በኃላ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሶስት ህዝበ ውሳኔዎችን እና አገራዊ ምርጫን የመሩት ወ/ሪት ብርቱካን ጤናዬን በሚገባ ለመጠበቅ ረጅም ጊዜ እረፍት ያስፈልገኛል ሲሉ በግል ማህበራዊ ገፃቸው ላይ በማስፈር የስንብት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዋና ሰብሳቢዋ መልዕክታቸውንም ሲያገባድዱ አብረዋቸው ለሰሩ የተቋሙ ሰራተኞች እንዲሁም ለፓርቲዎች እና አመራሮቻቸው ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የፖቲካ ፓርቲ አመራሮች በተለይም የኢዜማ፣የኦፌኮ፣የኢህአፓ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ አድርገዋል በቆይታቸውን ሀሳባቸውን አካፍለውናል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በወይዘሪት ብርቱካን ዙሪያ ምን አሉ?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ ፈይሰል አብዱላዚዝ ተከታዩን ብለውናል፤
አቶ ፈይሰል ወይዘሪት ብርቱካንን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያደንቋቸውና በመሀላቸው በርካታ ጊዜ አለመግባባት ተፈጥሮ የሚያውቅ ቢሆንም በስራቸው ሀገራቸውን በበጎ ማገልገላቸውን ይመሰክራሉ፡፡
በአቋማቸው የሚፀኑ፣ላመኑበት የሚታገሉ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም ለመገንባት የሚተጉ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
ስለለቀቁበት ጉዳይ ሲያብራሩም እንደ ጋራ ምክር ቤት መወያየት የሚጠይቅ ቢሆንም በጤና ምክንያት ለቀቁ የሚለው የማያሳምን ነው፣ በተቻለ አቅምም ሀሳባቸውን ለማስቀየር ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡
ተቋሙ በተቻለው መጠን ነፃ እና ገለለትኛ ለመሆን ይሰራ የነበረ መሆኑም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፣
ምርጫ ቦርድ ጥሩ የመለወጥ አዝማሚያ ያሳየበት ጊዜ እንደነበርና በትክክል ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል አቋም ላይ ደርሷል ባይባልም ውስጣዊ ሪፎርሙና አጠቃላይ የዲሞክራሲ ግንባታ በተለይ የብዙሀን ፓርቲ አደረጃጀት ላይ ያሳየው የስራ ትጋት የሚደነቅ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ከስራ መልቀቃቸውን በተመለከተ ሲያብራሩም ለመልቀቃቸው ያቀርቡት ምክንያት አጠራጣሪ ነው ያሉት ደ/ር ጫኔ፣ በቅርቡ እያየነው ያለው የመንግስት አካሄድ ለስራዎቿ እንቃፋት እንደሚፈጥሩባት እንዲሁም በተቋሙ በርጫ ቦርድ ላይ ጭምር ጫና እንደሚፈጥር በመገንዘብ የወሰኑት ውሳኔ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
ምርጫ ቦርድ በሪፎርሙ ላይ ጠንካራ ጎን ነበርው የሚሉት ዶ/ር ጫኔ ራሱን ሪፎርም አድርጎ የተንቀሳቀሰበት አካሄድ ጠንካራ ነው፣ በዚህም አንድ ብሔራዊ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን በተሳካ መንገድ መመራታቸውን እንደ በጎ ጎናቸው የሚነሳ ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ምን አሉ?
ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገለልተኛና ጠንካራ ቢሆኑም ስልጣን ላይ የወጡበት መንገድ ልክ ባለመሆኑ እዚህ ዉሳኔ ላይ ደርሰዋል ብለዋል፡፡
የፓርቲ መሪ የነበሩት ብርቱካን በሹመት የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሲሾሙ ጥያቄ ነበረን የሚሉት አቶ ሙላቱ፣ ለነፃነት ሲሟገት የነበረን አካል የመንግስት ተቋም ላይ በነፃነት እንደማይሰሩ ቀድሞውኑ አውቀን ነበር ብለዋል፡፡
የለቀቁበትን ምክንያት በተመለከተ የግል ምልከታቸውን ሲያስቀምጡም፣
ህዝብ በሚፈለግው መንገድ ምርጫ ማከናወን ስላልተቻለና የመንግስት ጣልቃ ገብነት አላሰራ ስላለቸው የለቀቁ እንደሚመስላቸው ተናግረዋል፡፡
ተቋሙን በተመለከተ እንደ አቶ ሙላቱ ገለፃ፣ ስርዓቱ እንጂ ግለሰቦች አይደልም ይላሉ፣ ስርዓቱ ነፃና ዲሞክራቲክ መሆን ስላልቻለ ማንም ሰው ቢመጣ ሊቀጥል አይችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ኢህአፓ ተቀደሚ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም ኃይማኖት ምን አሉ?
ምርጫ ቦርድ በዚህ አራት ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋም ለመገንባት ተሰርቷል ሲሉ ያነሳሉ፡፡
በተለይም ደግሞ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የነበራቸው ግንኙነት በቀናነት የሚታይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የለቀቁበት ምክንያት?
እንደ ኢህአፓ በጤና ለቀቁ የሚለው አይዋጥልንም የሚሉት አቶ አብርሃም ከበስተጀርባ የሆነ ሀይል እየገፋቸው መሆን አለበት አለበት ምን አልባትም ይህ ሁኔታ ወደፊት ይፋ ይሆናል ብለን እናስባለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስለ ተቋሙ፤
በተወፀነ መልክ በገዢው ብልፅግና ፓርቲ ተፅዕኖ ውስጥ እንደነበር ይታወቃል ያሉት ተቀዳሚ ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ወቅትም ገለልተኛ ያልሆኑ በመንግስት አካል የሆኑ ታዛቢዎችን ማሳተፍ የመሳሰሉትን እንቅስቃሴዎች ለመቅረፍ ፈጣን የሆነ ምላሽ መስጠት አልቻሉም፣ ከእነዚህ ውጪ ተቋሙ በወይዘሪት ብርቱካን ስር በጎ አመታትን አሳልፏል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በገዢዉ ፓርቲና በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ብዙ ተስፋ የተጣለባቸዉ ተቋማት ገና መሰረት መያዝ ሲጀምሩ አመራሮች ላይ ጫና በማድረግ ከስልጣን እንዲወርዱ እየተደረገ ነዉ የሚሉት እነዚህ የፓርቲ አመራሮች፣ ይህ ደግሞ ጠንካራ ተቋማት ለመገንባትያለዉን ህልም የሚያጨልም ነው ብለዋል፡፡
በአቤል ደጀኔ
ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም
