ጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ የድንገተኛ ህክምና ባለሙያዎችን አስመርቋል።

የጠብታ አምቡላንስ እህት ኩባንያ የሆነው ጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ ለ 2 ዓመት ያሰለጠናቸውን 55 ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመርቋል።

ኮሌጁ ያለምንም ክፍያ ያስተማራቸውን ተማሪዎች በሁለተኛ ዙር እያስመረቀ መሆኑን የኮሌጁ ዲን አቶ ስለሺ ሞላ ገልፀዋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 26ቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 5 ሆስፒታሎች የተመለመሉ መሆናቸውንም አቶ ስለሺ አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶ/ር ሙሉጌታ እንዳለ በበኩላቸው የድንገተኛ አደጋ በአለም ደረጃ በአመት ከ5 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወት ይቀጥፋል ያሉ ሲሆን ከ40-60 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ቋሚ የአካል ጉዳት ያጋጥማቸዋል ብለዋል።

ስለሆነም የድንገተኛ አደጋ ከባድ ጉዳት በሚያደርስበት በዚህ ጊዜ የድንገተኛ ህክምና ባለሙያዎች ቁጥር ከዚህ በላይ መጨመር እንዳለበት አንስተዋል።

ቅድመ ጤና ተቋም የህክምና አገልግሎትን ለማስፋት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

ኮሌጁ የስልጠና ሂደቱን ለመከወን 12 አሰልጣኞች እና 2 ረዳት አሰልጣኞች እንዲሳተፉ ማድረጉን የገለፁት የኮሌጁ ዲን ተማሪዎቹ ለ2 ዓመትም የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ጠብታ ፓራሜዲክ ኮሌጅ በ2010 ዓም ከኖርዌይ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የተመሠረተ የድንገተኛ ህክምና ማሰልጠኛ ተቋም ነው።

በእስከዳር ግርማ

ሐምሌ 01 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *