የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት፣የሀገሪቱ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ኃብቶች ለመጠቀም ባለሙያዎችን መልምለን ወደ ሥራ አስገብተናል ብለዋል።
የሀገሪቱን ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ኃብቶችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ምሁራንን በማደራጀት የባለሙያዎች ቋት መዘጋጀቱንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ወደ ቋት የገቡት ባለሙያዎቹ በውሃ ምህንድስና፤በህግ፤በዲፕሎማሲና በኮሙኒኬሽን ዘርፍ ልምድ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በድንበር ተሻጋሪ የውሃ ኃብቶች ላይ ይሰሩ የነበሩት ባለሙያዎች ባልተቀናጀ መንገድ ይሰሩ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣አሁን ግን በየሙያቸው በቂ ግንዛቤና ዕውቀት ኖሯቸው በአለም አቀፍ መድረክ ላይ የሀገራቸውን ጥቅም እንዲያስጠብቁ ይደረጋል ብለዋል።
ባለሙያዎቹን በማስተባበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን የድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን ጥቅም ለማስጠበቅ እንሰራለን ብለዋል ሚኒሰትሩ።
የአሁኑ የባለሙያዎች ቡድን በውሃና ኢነርጂ ላይ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች የተካተቱበት እንደሆነም ሰምተናል።
ላለፉት 10 ዓመታት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው የባለሙያዎች ቡድን ትልቅ ተሳትፎ ሲያደርግ እንደነበር የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጅ ይህ የባለሙያዎች ቡድን ለተወሰኑ ጊዚያት ተበትኖ ከቆየ በኋላ በአዲስ መልክ መቋቋሙ አይዘነጋም።
በአባቱ መረቀ
ነሃሴ 02 ቀን 2015 ዓ.ም
