ሴቶችን በግጭቶች ወቅት ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት መከላከል እንደሚገባ ጥምረት ለሴቶች ድምፅ አሳሰበ።

እንደ ሀገር በትግራይ በተፈጠረው ግጭት ካጋጠመው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በአግባቡ ሳናገግም፣ በአኹኑ ወቅት ደግሞ በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተው ወቅታዊ የፖለቲካ እና የፀጥታ ቀውስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ አሳዛኝ ነው ሲል ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በተጨማሪም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ግጭቶች በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም የሚታዩ ሲኾን፣ በእነዚህ የሰላም መደፍረሶች ውስጥ ሴቶች ዋነኛ ተጠቂዎች መኾናቸው አሳስቦኛል ብሏል።

በመኾኑም እዚኽም፣ እዚያም የሚታዩት ችግሮች ወደተባባሰ ሀገራዊ ቀውስ ከመሸጋገራቸው በፊት በሰላማዊ ውይይት እንዲፈቱ በአጽንኦት ጠይቋል።

ይኽንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ጥምረቱ ከሚያቀርበው የሰላም ጥሪ በተጨማሪ፣ የሚከተሉት ሐሳቦች በሰላም ማስከበር ሂደት ውስጥ እንዲተገበሩ እንጠይቃልን ብሏል፡፡

  1. ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲከበሩ አጽንኦት እንዲሰጠዉ።
  2. ጥቃትን መከላከል እና የመብት ጥበቃ ሴቶችን በትጥቅ ግጭቶች ወቅት ከማንኛውም ዓይነት ጥቃት መከላከል እንደሚያስፈልግ።

3.በሁሉም የሰላም እና የፀጥታ ማስከበር ሂደቶች ላይ የሴቶችን የነቃ ተሳትፎ ማበረታት አለብን ብለዋል በመግለጫቸዉ።

ከዚህ ባሻገር ሴቶች ድምፃቸው እንዲሰማ፣ ሐሳባቸው በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ጎልቶ እንዲታይ፣ በማንኛውም ሰላማዊ ድርድሮች እና የፀጥታ መዋቅሮች ውስጥ በጎ ተፅዕኖ እንዲኖራቸው እንጠይቃለን ብለዋል።

ጥምረት ለሴቶች ድምፅ በሀገራዊ ምክክር መድረክ መጋቢት 2014 ዓ.ም ሴቶች በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ተገቢ ውክልና እንዲኖራቸው ለማስቻል የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ50 በላይ አባል ድርጅቶችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በአቤል ደጀኔ

ነሃሴ 08 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *