በትግራይ ክልል ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆን የእርሻ መሬት በአንበጣ መንጋ መወረሩን የክልሉ የግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በትግራይ ክልል በሶስት ዞኖችና በ17 ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ዘጠኝ ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ሲሆን ከ80 በመቶ በላይ የእርሻ መሬቶች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገልጿል፡፡

ከሐምሌ 22 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከአፋር ክልል ዘጠኝ ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የአንበጣ መንጋ መግባቱና እህሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ለጣብያችን አስታውቋል፡፡

ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ የነበራቸው የክልሉ የግብርና ቢሮ የአዝርት ጥበቃ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መብራህቱ ገብረኪዳን ከአፋር አካባቢ የሚመጣው የአንበጣ መንጋ በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡

የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋት ከፍተኛ የሆነ ርብርብ እየተደረገ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ በሰው ሀይል በመጨፍጨፍ እንዲሁም የተወሰኑ የኬሚካል ርጭት በማከናወን የማጥፋት ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ከፌደራል መንግስትም ሆነ ከክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር የተወሰነ ድጋፍ የተደረገ ቢሆንም በቂ አለመሆኑና ከተጠየቀው 19ሺህ ሊትር ኬሚካል የቀረበው 7ሺ ሊትር ብቻ በመሆኑ ያለውን በሙሉ ተጠቅመን በመጨረሳችን ተቸግረናል ሲሉ ለጣብያችን ተናግረዋል፡፡

አቶ መብራሃቱ የአንበጣ መንጋውን መስፋፋት ለመግታት መንግስት በአፋር ክልል ያለውን የአንበጣ መንጋ በአውሮፕላን ርጭት ማጥፋት ከተቻለ መስፋፋቱን ሊገታው ስለሚችል እዚህ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ክልል ለተከሰተው “እጅግ አስከፊ” የአንበጣ መንጋ የክልሉ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚፈልግ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

በአቤል ደጀኔ
ነሃሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *