እየተገነባ ባለ አፓርታማ ላይ የተከሰተ የእሳት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ፡፡

ትላንት መስከረም 14 2016 ዓ.ም ምሽት 1:05 ሰዓት ላይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ሀጫሉ ሁንዴሳ መንገድ ትራኮን ሪል እስቴት እየገነባ ባለዉ አፓርታማ 5ኛና 6ኛ ፎቅ ላይ የተነሳዉ የእሳት አደጋ በሁለት ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ሲያደርስ በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት አድርሷል።

አደጋዉ የደረሰባቸዉ ሁለቱም የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሲሆኑ አንደኛዉ ሰራተኛ እሳቱን በማጥፋት ሂደት ከህንጻዉ ላይ ወድቆ ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በአሁን ሰዓት በአለርት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት ይገኛል ተብሏል።

የእሳት አደጋዉ በአካባቢዉ ባሉ መኖሪያ ቤቶች ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር 9 ሰዓት ፈጅቷል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር የዉሀ ቦቴዎችን ጨምሮ 18 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች ከ94 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶችና የአዲስ አበባ ዉሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ዉሀ የጫኑ ቦቴዎችን በማቅረብ ድጋፍ አድርገዋል።

መረጃው፡-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነው፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *