ቃል የተገባለትን ገንዘብ ማገኘት ባለመቻሉ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ህብረተሰቡ ለመቀላቀልና ለማቋቋም አለመቻሉን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ ከስምንት ክልሎች የተወጣጡ 3መቶ 71ሺህ 9መቶ71 የቀድሞ ተዋጊዎች በስሩ ያሉ ቢሆንም አንድም ተዋጊን ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀል አልመቻሉን ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል፡፡

ስራው ሲጀመር የቀድሞ ታዋጊዎችን በሶስት ምዕራፎች ወደ ህብተሰቡ ለመቀላቀል ታስቦ እየተሰራ ነበር የሚሉት የብሔራዊተሃድሶ ኮሚሽን የኮሚኒኬሽንና ዓለም ዓቀፍ ትብብር ዳይሬክተር አቶ ልዑል ሰገድ በላይነህ በመጀመሪያ ዙር 50ሺህ ታዋጊዎችን ፣በሁለተኛ ዙር ደግሞ 175ሺህ እንዲሁም በሶስተኛ ዙር ቀሪ ተዋጊዎችን በአንድ ግዜ ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በበጀት እጥረት ምክንያት አለመሳካቱን ተናግረዋል፡፡

በስምንት ክልሎች በተለይም በርካታ የቀድሞ ታዋጊዎች ያሏቸው ትግራይ፣አማራ እና ኦሮሚያ ያሉ ተዋጊዎችን ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ ታስቦ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ የልማት አጋሮች እንዲሁም ጦርነቱ እንዲቆም ከፍተኛ ጥረት ሲያደረጉ ከነበሩ ሀገራት ጭምር ቃል የገቡትን ገንዘብ መለገስ ባለመቻላቸው ስራውን ለመግፋት መገደዳቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር 50ሺህ ገደማ የቀድሞ ታዋጊዎችን ወደ ህብረተሰቡ መመለሳቸውን መናገሩ የሚታወስ ቢሆንም ተዋጊዎቹ በራሳቸው ፍላጎት የተመለሱ እንጂ የተሃድሶ ፕሮግራም ወስደው የወጡ አለመሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የተወሰኑ ሀገራት በ2024 አዲስ ዓመት ጀምሮ የኮሚሽኑን ስራ በዕቅዳቸው በማስገባት ድጋፍ ለማድረግ ማሰባቸው በቀጣይ በትልቅ ተስፋ የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በቅረቡ ከኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ የፈረመው ኮሚሽኑ በቀጣይ ከሌሎች ተቋማት ጋርም በጋራ በሚሰራባቸው ሁኔታዎች ላይ ትብብር እንደሚፈጥር አስታውቋል፡፡

በአቤል ደጀኔ

ጥቅምት 08 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *