የድሬደዋ መካነ-እየሱስ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ቤተክርስቲያኗ ትፍረስ በሚል ያወጣውን ውሳኔ በ2 ቀን ውስጥ እንዲያስተካክል ጠየቀች፡፡

የድሬደዋ መካነእየሱስ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀችው፣ ቤተክርስቲያኗ ለ40 አመታት በስፍራው የቆየች እና ህጋዊ ይዞታ ቢኖራትም የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ግን በአንድ ወር ውስጥ ከቦታው እንድትነሳ ለቤተክርስቲያኗ ደብዳቤ ልኳል፡፡

የከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት ለቤትክረስቲያኗ በላከው ደብደቤ እንዳስቀመጠው፣ ቦታው ለሆቴል ቱሪዝም በመፈለጉ መሆኑን የቤተክርስቲያኗ ዋና ሰብሳቢ ቄስ በላቸው አምባሮ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የትውልድን ስነምግባር የምትቀርጽ እና በይዞታዋም ህጋዊ የሆነችን ቤተክርስቲያን አፍርሶ ሆቴል መስራት አግባብነት የሌለው እና በምዕመን መካከል ሁከትን መፍጠር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያኗ ለከተማዋ መንገድ ስራ በሚል ተባበሪ በመሆን የተወሰኑ ሜትሮችን ወደ ውስጥ ተጠግታለች ያሉት ቄስ በላቸው፣ ይህ ግን በህልውናዋ ላይ የመጣ ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም የከተማዋ ከንቲባ ጽ/ቤት ካቢኔ የወሰነውን ውሳኔ በሁለት ቀን ውስጥ እንዲያስተካክል የጠየቀች ሲሆን፣ይህ ካልሆነ ግን ቤተክርስቲያኗ ሌሎች ህጋዊ አማራጮችን እንደምትጠቀም አንስተዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም ጉዳዩን ለማጣራት የድሬደዋ ከተማ ከንቲባ ጸህፈት ቤትን የጠየቀ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኗ እንድትፈርስ ካቢኔው ወስኖ ለቤተክርስቲያኗ ደብዳቤ ተልኳል ሲሉ የጽ/በቱ ሃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ነግረውናል፡፡

ቦታው ለልማት ተፈልጎ ነው ያሉት ሃላፊው፣ ካቢኔው የልማት ጥያቄዎችን የማስተናገድ ሃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ጉዳዩን ተቃውማ ደብዳቤ ከመላክ ይልቅ ቤተክርስቲያኗ ከጽ/ቤቱ ጋር አልተነጋገረችም ያሉት ሃላፊው ፤ሁሉም ነገር የሚፈታው በንግግር ነው ብለዋል፡፡

በመሳይ ገ/መድህን

ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.