ከሁለት አመት በፊት ግንባታው የተጀመረው የሚዛን አማን አየር ማረፍያ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ግንባታው መስተጓጎሉ ነው የተነገረው፡፡
የሚዛን አማን አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ጋስካር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ለፕሮጀክቱ ከቦታቸው ለተነሱ ባለይዞታዎች እስካሁን ካሳ አልተከፈላቸውም ብለዋል፡፡
እስካሁን ለአየር ማረፊያው ግንባታ ከ107 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ በመክፈል 126.9 ሄክታር ቦታ ከይገባኛል ነጻ ተደርጎ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ ካሳ ሳይከፈላቸው በትዕግስት ጠብቀዋል ያሉት አቶ ተስፋዬ ግለሰቦቹ ከቦታው ንብረታቸውን አንስተው ባዶ እጃቸው ተቀምጠዋል ብለዋል፡፡
በ2013 በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የመሰረት ድንጋዩ የተጣለው የሚዛን አማን አየር ማረፍያ ግንባታ በሁለት አመት ተኩል ይጠናቀቃል ቢባልም እስካሁን ግንባታው በተባለው ጊዜ ሊጠናቀቅ አለመቻሉ ነው የተገለጸው፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ጉዳዩን በቅርበት ተከታትሎ መፍትሔ እንዲፈልግ ጥሪ ቀርቦለታል።
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም
