“የፕሪቶርያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲከበር አሁንም ቁርጠኛ ነኝ” –መንግስት

የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነትን አንደኛ ዓመት በተመለከተ የኢፌዴሪ መንግሥት መግለጫ አውጥቷል

በመግለጫውም በትግራይ ከሁለት ዓመታት በፊት የተፈጠረው ሁኔታ ወደ ጦርነት ከማምራቱ በፊት መንግሥት የሰላም አማራጮችን ሁሉ መሞከሩን እስታውቋል፡፡

በትግራዩ ጦርነት የደረሰውን ኪሣራ ከትግራይ ሕዝብና ከክልሉ መንግሥት በላይ የሚያውቀው የለም ያለው መግለጫው ጦርነትን ብቸኛ አማራጫቸው ያደረጉ ኃይሎች የትግራይን ወጣቶች ለእሳት ማግደዋቸዋል፤ የኢትዮጵያን እናቶች በኀዘን እሳት ጠብሰዋቸዋል፤የክልሉን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ አውድመዋል ብሏል፡፡

በጦርነቱ መጨረሻ የፌዴራል መንግሥት ሁሉን ነገር በኃይል ለመፈጸም የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና ነበረው፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ቢቋጭ ሀገርን አትራፊ የሚያደርግ መሆኑ ስለታመነበት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም አድርጓል ነው ያለው፡፡

አከራካሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ አቋም ወስዶ ሠርቷል ያለው መግለጫው የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም ወገን በሚጠቅም መንገድ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ብልጽግና በሚያረጋግጥ መንገድ መፍትሔ መሰጠት አለበት የሚል እንደሆነም አስገንዝቧል፡፡

ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፤ የአካባቢ ነዋሪዎች በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ፤ በመጨረሻም ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ይሄንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝና ይህ ሁሉ ቢደረግም በዚያኛው ወገን እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል ነው ያለው፡፡ ይህ ግን ዘላቂ ሰላምን፣ ብልጽግናንና የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አያረጋግጥም ያለው መግለጫው የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶርያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ መጓዙንና በዚህም ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ደጋግሞ ማሳየቱን መግለጫው ያትታል፡፡

የፕሪቶርያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ _ እንዲከበር መንግሥት አሁንም ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ያመለከተው መግለጫው ሁሉም አካላት ተመሳሳይ ቁርጠኝት በማሳየት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባልም ብሏል፡፡

ኢት ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *