በትግራይ ክልል የህክምና መድሃኒቶች እጥረት መከሰቱ ተነገረ፡፡

በተለይም በክልሉ በተከሰተዉ የወባ ወረርሺኝ ምክንያት የወባ በሽታ መድሃኒት ከፍተኛ ዕጥረት መኖሩን ሰምተናል፡፡

ከወባ መድሀኒት በተጨማሪ ደግሞ የኤችአይቪ መመርመሪያ ፤ የጸረ ካንሰር መድሃኒቶችና ለኩላሊት ዕጥበት የሚያገለግሉ የላቦራቶሪ ግብአቶች በከፍተኛ ሁኔታ ክልሉ ላይ ችግር ሆነዉ ቀጥለዋል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የመቀሌ ቅርንጫፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሄዋን ሰመረ ለኢትዮ ኤፍኤም እንደተናገሩት፤ ከፍተኛ የመድሃኒት ፍላጎት ቢኖርም አቅርቦቱ ዝቅተኛ ነዉ ብለዋል፡፡

መድሃኒቶችን በጠየቅነዉ መሰረት ማግኘት ስለማንችል ለጤና ጣቢያዎቹም በጠየቁት መሰረት መድሃኒቶችን እያቀረብን አይደለም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ከጦርነቱ በፊት እንደነበረዉ ወደ ሲስተም ገብተን ተቋሙም በልዩ ሁኔታ መድሃኒቶችን እያቀረበልን ቢሆንም አሁንም አቅርቦቱ በቂ አይደለም ብለዉናል፡፡

ምክትል ስራ አስኪያጇ ከዋናዉ የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎትም ዕጥረት በመኖሩ ምክንያት እነዚህን መድሃኒቶችን እንደ ልብ ማግኘት አለመቻላቸዉን ነግረዉናል፡፡

በእስከዳር ግርማ

ሕዳር 07 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *