በዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችሉ ምርቶችን ወደ ግብይት ስርዓቱ ለማስገባት ጥናት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህን ያለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ነው፡፡
ተቋሙ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ቡናን ጨምሮ ከ23 በላይ የግብርና ምርቶችን ሲያገበያይ መቆየቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ዳዊት ሙራ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስካሁን ድረስ የመጣበት መንገድም በግብርና ምርቶች ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር ያሉት አቶ ዳዊት፣ አሁን ላይ የኢንዱስትሪ ግብዓት ምርቶችንም ወደ ግብይት ስርዓቱ ለማስገባት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸውልናል፡፡
በተጨማሪም በሲሚንቶ እና በማድናት ግብይት ስርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮችን አስቀድሞ በጥናት የመለየት ስራ ተቋሙ እየሰራ እንደሚገኝም ሃላፊው አንስተዋል፡፡
እየተደረገ ያለው ጥናት በዚህ አመት ይጠናቀቃል ያሉም ሲሆን፣ ከጥናቱ በኋላ የተባሉት ምርቶች ወደ ገብይ ስርዓቱ እንደሚገቡ አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ለሁሉም የምርት አይነቶች የሚሆን የዲጅታል የግብይት ስርዓት እየተዘረጋ በመሆኑ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በግብርና ምርቶች ብቻ አይገደብም ነው ያሉት፡፡
ከተመሰረት 15 አመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ በግብርና ምርት የግብይት ሰንሰለት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በተወሰነ ደረጃ ቢያስቀርም አሁንም ራሱን በሚገባ በመፈተሽ ከዘመኑ ጋር ሊራመዱ የሚችሉ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባው ተጠቁሟል፡፡
በመሳይ ገ/መድህን
ህዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም
