እግረኞች፣ሞተረኞች እና ሳይክል ተጠቃሚዎች ለትራፊክ አደጋ ቀዳሚ ተጋላጭ መሆናቸዉ ተገለፀ።

በ2015 ዓ.ም 393 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸዉ ማለፉ የተገለፀ ሲሆን ከ2014 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር የ7.5 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱም ተገልፃል።

ይህ የተገለፀዉ በዛሬዉ ዕለት በትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን እና በብሉምበርግ ኢኒሼዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ አጋር ድርጅት ከሆነው ቫይታል ስትራቴጂስ ጋር በመተባበር በፍጥነት ማሽከርከር ላይ ያተኮረ እና ‘’ፍጥነት ይገድላል፤ በዝግታ ያሽከርክሩ!’’ በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ከተማ አቀፍ የብዙኃን መገናኛ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ነዉ።

የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች በርካታ ቢሆንም ፍጥነት ዋነኛዉ መሆኑን የገለፁት የባልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበዉ ሚደቅሳ ከዘጠኝ ዓመት በላይ የመንገድ ስትራቴጂ በመንደፍ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዓለም ላይ 40 በመቶ የሚሆነዉ የትራፊክ አደጋ ከፍጥነት ጋር በተያያዘ በመሆኑ ፍጥነት ላይ አተኩሮ መስራቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል።

በዓለም ደረጃም ሆነ እንደ ሀገር በእግረኞች፣ሳይክል ተጠቃሚዎች እና ሞተረኞች ላይ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ እንደሚከሰተም ተገልጿል።

የቫይታል ስትራቴጂ የአፍረካ ቅርጫፍ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል ሞላ በበኩላቸዉ በዚህ ንቅናቄ በሀገር አቀፍ ደረጃ የህግ ማዕቀፍ እንዲፈተሽ ለመጠየቅ የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይም በብሉመበርግ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በ2015 ዓ.ም ከፍጥነት ጋር በተያያዘ ጥናት ቀርቧል።

በጥናቱም 80 በመቶ የሚሆነዉ የሞት አደጋ ላለፉት ስምንት ዓመታት እግረኞች ላይ እንዳጋጠመ ተገልፃል።

ከዚህ ባለፈም ቅዳሜ በርካታ የሞት አደጋ የሚደርስበት ቀን ሲሆን ማታ ከ12 አስከ 2 ሰዓት ያለዉም በርካታ አደጋ የሚያጋጥምበት ሰዓተ መሆኑ ተነስቷል።

ቦታን በተመለከተም መገናኛ ቀዳሚዉ የትራፊክ አደጋ የሚደርስበት አካባቢ በመሆንም ተለይቷል።

የብዙኃን መገናኛ ንቅናቄው ለ4 ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን በፍጥነት ማሽከርከር ላይ ያተኮሩ መልዕክቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ በህትመት ውጤቶች እና ሌሎች የመልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴዎች አማካኝነት እንዲተላለፉ ይደረጋልም ተብሏል፡፡

በአቤል ደጀኔ
ህዳር 25 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.