የኢንሹራንስ ዘርፉን ይደግፋል የተባለ ፕሮግራም ወደ ስራ ገብቷል።

ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች በፈጠራ የታገዙ የኢንሹራንስ መፍትሄዎች ያላቸውን አስፈላጊነት መሠረት አድርጎ ወደ ስራ እንደገባም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ላለው የኢንሹራንስ ዘርፍ ድጋፍ ያደርጋል የተባለ “ቢማላብ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ፕሮግራም በኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ አማካኝነት ወደ ስራ መግባቱ ነው የተገለፀው።

በፕሮግራሙ በኢንሹራንስ ዘርፍ ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ መፍትሔዎችን እና ፈጠራዎችን በማጎልበት ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ ለማምጣት ታቅዷል ነው የተባለው።

ቢማላብ ኢትዮጵያ የፈጠራ ባለቤቶች የሆኑ ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች የሚገጥሟቸውን የፋይናንስ እና የሰለጠኑ ባለሙያዎች ዕጥረት እና መሠል ችግሮችን የሚፈቱበትን መንገድ ለማሳየት ያለመ ነውም ተብሏል።

ይህ ፕሮግራም ሁሉን አቀፍ የፋይናንሻል መፍትሄዎችን ለማምጣት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉ በኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አቤል ታደለ ተናግረዋል።

ቢማላብ ኢትዮጵያ በጅምር ያሉ የፈጠራ ሀሳቦች ከታገዙ በኢንሹራንስ ዘርፍ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ ለማድረግ ያለመ ነው ያሉት አቶ አቤል ፤ በኢንሹራንስ ዘርፍ ውስጥ ያሉ አካላት አሁን በአገራችን ያለውን የዲጂታል ፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት በመጠቀም ተደራሽነታቸውን ማስፋት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

ፕሮግራሙ ላይ የሚሳተፉ 15 ጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች የተመረጡ ሲሆን ከዚህ መሃል አራት የሚሆኑት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ናቸው።

በመጀመሪያ በኤፍኤስዲ አፍሪካ በአህጉር ደረጃ ተተግብሮ  በኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ አማካኝነት ወደ ስራ የገባው “ቢማላብ ኢትዮጵያ” በቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የገንዘብ ድጋፍ የተጀመረ ነው።

እስከዳር ግርማ

ህዳር 26  ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.