የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማስታወቂያዎችን ለማዘመን በሚል የቢልቦርድ ማስታወቂያዎች እንዲነሱ መመሪያ ማውጣቱ ተገቢ አይደለም ተባለ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ማስታወቂያዎችን ማዘመኑ ተገቢ ቢሆንም የቢልቦርድ ማስታወቂያዎችን በማስቀረት በዲጂታል ስክሪኖች ይተኩ መባሉን የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ማህበር ተቃውሞታል።

ማህበሩ ማስታወቂያዎች እንዲዘምኑ እየሰራ መሆኑን ገልፆ፣ ይሁን እንጅ ከተማ አስተዳደሩ ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሲል ተቃውሟል።

የከተማ አስተዳደሩ ማስታወቂያዎች በዲጂታል ስክሪን መተላለፍ አለባቸው ከማለቱ በፊት የውይይት መድረክና ጥናት ላይ የተመሠረት ውሳኔ ማሳለፍ ነበረበት ብሏል ማህበሩ።

የማስታወቂያዎችን መዘመን እንደሚደግፍ የገለፀው ማህበሩ ይሁን እንጅ ከተማ አስተዳደሩ ከግንዛቤ ሊያስገባቸው የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ አንስቷል።

ማህበሩ እንደ ስጋት ካነሳቸው መካከል በከተማዋ ያለው የኃይል አቅርቦት ፣የትራፊክና ከእይታ አንፃር የጤና ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚሉት ይገኙበታል።

የከተማ አክተዳደሩ በህገወጥ መንገድ በየጎዳናዎች ላይ የሚለጠፉ ህገወጥ ማስታወቂያዎችን እንዲቆጣጠርም ተጠይቋል።

ማስታወቂያዎች የከተማዋን ውበት በጠበቀ መልኩ እንዲሰሩ ከተፈለገ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረግ እንዳለበት ማህበሩ ጠይቋል።

ከተመሠረተ አራት አመት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ማህበር ማስታወቂያዎችን ለማዘመን እንደሚሰራም አስታውቋል።

በአባቱ መረቀ

ታህሳስ 04 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *