ለባህላዊ ህክምና የሚውሉ ግብዓቶችን በላብራቶሪ የመመርመር ስራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ይህንን ለማድረግ ግን ቅድሚያ የባህል ሀኪሞቹ እውቅና ያስፈልጋል ስለመባሉ ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀድም የምርመራ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለፁልን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የጤና ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር የሆኑት ሲስተር በድሪያ ሁሴን ናቸው፡፡

እንደሳቸው ሀሳብ በሚኒስትር መስሪያ ቤት ደረጃ የባህል ህክምና ግብዓቶች ላይ የጥናትና ምርምር ለማከናወን ሂደት ላይ መሆኑን ለጣብያችን ተናግረዋል፡፡

ባህላዊ ህክምናን በተመለከተ ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲሰራጭ የነበሩ በተለይም ከህክምናው የወጡ አሰራሮች ሲያወዛግቡ መክረማቸውን የሚገልፁት ሲስተር በድሪያ ተቋማቸው ባካሄደው የመስክ ምልከታ በአዲስ አበባ ከተባለው ነገር ጋር ወይም በህገወጥ አሰራር ጋር በተገናኘ የተጠየቀ የባህል ህክምና ተቋም አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

በሶሻል ሚዲያ የሚጠቀሱ የህክምና ምርምራ ዓይነቶች ከኛ መስፈርት ውጪም ነው ያሉት ዳይሬክተሯ ከዚህ ጋር በተያያዘም ዕውቅና አንሰጠም ብላዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚሰራጩ የባህል ህክምና አገልግሎት እንሰጣለን ከሚሉት መካከል ለስልጣን፣ ለግርማ ሞገስ፣ ትዳር እምቢ ላለው፣ ወደ ውጭ ለሚጓዝ፣ ሎተሪ እንዲደርሳችሁ ፣ለቤቲንግ እና ለእቁብ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

አንድ የባህል ህክምና አዋቂ ተቋም ከፍቶ ለመስራት የሚያስብ ከሆነ ቢያንስ በአንድ አካባቢ ለሶስት ዓመታት የኖረ እንዲሁም ሶስት ክፍል ያለው ህንፃ ሊኖረው ይገባል ተብሏል፡፡

በመሆኑም በአዲስ አበባ አሉ ተብለው በሶሻል ሚዲያ ላይ የሚሰራጩት የባህል ህክማና ቤቶች አለመኖራቸውን ዳይሬክተሯ በመግለፅ ነገር ግን ያልተመዘገቡ በህገወጥ መንገድ የሚሰሩ ካሉ ህብረተሰቡ ጥቆማ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከሳምንታት በፊት ” የባህል ህክምና እንሰጣለን የሚሉ አጭበርባሪ ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው ” ሲል የአ/አ ባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማህበር ስጋቱን መጥቀሱ አይዘነጋም፡፡

በአቤል ደጀኔ
ታህሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *