በገበሬ ስም ያወጡትን የአፈር ማዳበሪያ ለግል ጥቅማቸው በማዋል መምህራን ደሞዘ እንዳይከፈላቸዉ ያደረጉ 10 አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸዉ ተነግሯል

በከምባታ ዞን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በገበሬ ስም ያወጡትን የአፈር ማዳበሪያ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ የቀድሞ 10 አመራሮች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የወረዳው አስተዳደር ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል፡፡

አመራሮቹ በቀድሞ የደቡብ ክልል አስተዳደር ስር በታቀፈው የከምባታ ጠምባሮ ዞን ፤ከቀበሌ አንስቶ እስከ ወረዳ ድረስ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡

በአመራር ሃላፊነታቸው ወቅት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአፈር ማዳበሪያ ለገዛ ጥቅማቸው ማዋላቸውን ነው የልዩ ወረዳው አስተዳደር አቶ አበራ አፍሪጦ ለጣቢያችን የተናገሩት፡፡

ማዳበሪያው በብድር የመጣ በመሆኑ እንዲከፍሉ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ፍቀደኛ ባለመሆናቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የማዳበሪያው እዳ በጊዜው መከፈል ስላለበት ከመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ተቆራጭ መሆኑን አቶ አበራ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም የተነሳ ባለፉት ሁለት ወራት ለመምህራን የወር ደሞዛቸው በአግባቡ ሊከፈላቸው አልቻለም ብለዋል፡፡

ይህም አሁን ላለነው አመራሮች ከፍተኛ ፈተና ሆኖብናል ያሉት የልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አመራሮቹ ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የከምባታ ዞን የጠምባሮ ልዩ ወረዳ መምህራን ደሞዝ በአግባቡ እየተከፈለን ባለመሆኑ በከባድ የኑሮ ጫና ውስጥ እንገኛለን ሲሉ ለጣቢያችን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

መሳይ ገብረመድህን
ታህሳስ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *