ከ1 ሺህ 5 መቶ ኪሎ ግራም በላይ ህገወጥ ስጋ እንዲወገድ ማድረጉን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ፡፡

በከተማዋ ሰሞኑን በተሰራ ኦፕሬሽን 30 ህገወጥ ስጋ ይዘው የተገኙ ስጋ ቤቶች መያዛቸውን ጣብያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡

ከጣብያችን ጋር ቆይታ የነበራቸው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰኢድ ኢድሪስ በህገወጥ እርድ ላይ የተሰማሩ 15 ልኳንዳ ቤቶችን የማሸግ ስራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ በሶስት ቀን ውስጥ ብቻ 1500 ኪሎ ግራም ህገወጥ ስጋ ተስብስቦ እንዲወገድ መደረጉን አዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቋል፡፡

አቶ ሰዒድ በተደረገው ኦፕሬሽን በህገወጥ እርድ ላይ የተሰማሩ አካላት መያዛቸውን በመግለፅ ነገር ግን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ የመሸጥ ነገር ግን አለመኖሩን ለጣብያችን ተናግረዋል፡፡

ህገወጥ ስጋ የሚያጓጓዙ ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም ማረጃ ቦታዎችን የመለየት ስራ ተሰርቷል ያሉት ስራ አስኪያጁ በቀጣይ የህገወጥ እርድ የፈፀመው ተቋም ስም እየተጠራ የማጋለጥ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ነጋዴዎች ወደ ህገዋጥ እርድ የሚገቡት ግብርን ፍራቻ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ ይህንንም ለማስፈፀም ህገወጥ ደረሰኝ ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡

በዚህም ህገወጥ ደረሰኝ የሚጠቀሙ 10 ልኳንዳ ቤቶች መገኘታቸውንና የማሸግ ስራ መሰራቱን በመግለፅ በቀጣይ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለገና በዓል የቁም እንስሳት በበቂ ሁኔታ እየገባ መሆኑን የገለፀ ሲሆን 3 ሺህ ከብቶች እና 5ሺህ በጎች ለበዓል መዘጋጀታቸውን አስታውቋል፡፡

በአቤል ደጀኔ
ታህሳስ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *