ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን እድል ያገኘችበት ነው የተባለው ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ተቋሙ “ተልእኮውን ለማሳካት የሚያስችል እድል የተገኘበት ነው” ሲል የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ገለፀ።
በ2011 ዓ. ም በአዋጅ እንደገና የተቋቋመው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል 4 የቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መኮንኖች እያማከሩት፣ በፈረንሳይ ድጋፍ በሰው ኃይል ፣ በስልጠና እና በባሕር ልምምድ ራሱን ሲያደራጅ መቆየቱን ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላም እና የወጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል።
የባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ሪል አድሚራል ናስር አባዲጋ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሀገር ውኃ ላይ መንቀሳቀስ እንችላለን ብለን ሥንሠራ ቆይተናል።
በቅርብ ጊዜም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ በስምምነት ወዳገኘችው የባሕር በር ግዳጅ እንገባለን ብለን እናስባለን” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ኢትዮጵያ የንግድ መርከቦቿን ከአደጋ እንድትጠብቅ እና በቀጣናው ያለውን የሕገ ወጥ የመሣሪያ እና የሰዎች ዝውውርንም ለመከላከል ይሰራል ተብሏል ሲል የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም
