በስምንት ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ 1.8 ሚሊየን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ እና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት ይሰጣል ተብሉ ተስፋ የተጣለበት የወተር ፎር ላይፍ ፕላስ ” water 4 life +”ፕሮጀክት አመርቂ ውጤት እንዳላሰመዘገበ ተነግሯል፡፡
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባቀረበው የኦዲት ሪፖርት በስምንት ክልሉች ባሉ 10 ወረዳዎች በሁለት ምዕራፎች በመጠጥ ውኃ ፤ ከፀሐይ ለሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ጨምሮ ቀጣይነት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ለመስራት ቢታቀድም በተባለላቸው ልክ አልተሰሩም ተብሏል፡፡
የአምስት አመታት ቆይታ ጊዜ ነበረው የተባለው እና የ1 መቶ28 ሚሊየን ዶላር ባጀት የተያዘለት ይህ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ፤ በአማራ ፤በትግራይ ፤በሶማሌ ፤በአፋር ፤በቀድሞ የደቡብ ክልል፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ ክልሎች ላሉ አስር ወረዳዎች ውስጥ ነው ለመስራት የታቀደው፡፡
የዋተር ፎር ላይፍ ፕላስ ” water 4 life+ “ፕሮጀክት ለትምህርት ቤቶች ፤ለጤና ተቋማት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፤ሳኒተሸን እና ከፀሃይ ብርሃን ለሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ፕሮጀክት ቢቀርፅም፣ የታቀደለትን ያህል መጓዝ አልቻለም ብሏል የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፡፡
ፕሮጀክቱ እንዲከታተል ተቋቁሟል የተባለው ስትሪንግ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት በዚህ ፕሮጀክት የሁለት አመት ቆይታ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ከተቀመጠው 8 መቶ ሺህ የህብረተስብ ክፍሎች ውስጥ አገልግሎቱን ያገኙት 224 ሺ 359 ብቻ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በወርልድ ቪዝን በቀረበው ሁለት ሪፖርት የተቆፈሩት ጉድጓዶች ከፍተኛ የቁጥር ልዩነት ያላቸው መሆናቸው እንዲሁም የተቆፈሩትም ቢሆን የጥልቀት መጠናቸው የተቀመጠውን ስታርዳርድ የማያሟሉ ስለመሆናቸው ተገልጿል፡፡
ከዚህም ባሻገር 17 የውሃ ጉድጓዶች የፍሎራይድ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንደሌላቸው ተነግሯል፡፡
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በላከው ሪፖርት አጠቃላይ በሁለት ዓመታት የሚቆፈረው ጉድጓድ መጠን 97 ቢሆንም የተሠራው ግን 86 እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ስትሪንግ ኮሚቴው በበኩሉ ባወጣው ሪፖርት የተቆፈረው የውኃ ጉድጓድ 70 መሆኑን አስቀምጧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በተደረገው ማጣራት 11 ጉድጓዶች ደረቅ መሆናቸው መረጋገጡን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡
ለዚሁ ተግባር ተብለው በከፍተኛ ወጪ የተገዙት መሳሪዎችም ከስራው ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ብላል፡፡
በተደረገው ቆጠራም ተገዝተው ስራ ላይ ያልዋሉ 8436 ንብረቶችም መገኘታቸው ተነግሯል፡፡
አብዛኛዎቹ የግዢ ፍላጎት መግለጫ ሳይዘጋጅላቸው በዘፈቀደ የተገዙ ናቸውም ተብሏል፡፡
የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የገንዘብ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና የመብራት አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የትምህርትና የጤና ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ነዉ የተባለዉ፡፡
እንዲሁም የአካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ‹‹Child Inevestment Fund Action (CIFF)›› የተባለ በጎ አድራጎ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ ፕሮጀክት ቀረፆ መግባቱም ተጠቅሷል፡፡
በያይኔአበባ ሻምበል
ጥር 06 ቀን 2016 ዓ.ም
