የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ በዓለ ጥምቀትን አስመልክቶ በሀገረ ስብከታቸው ጽ/ቤት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል !

በመግለጫቸውም የጥምቀት በዓል ነጻነታችን የታወጀበት ፣ የዕዳ ደብዳቤያችን የተፋቀበት የባርነት ቀንበር የተሰበረበት ፣ የሚናፈቀው የእግዚአብሔር ድምፅ የተሰማበት ፣ ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ፣ ልጅነትን የምንቀበልበት ጸጋ የተመሠረተበት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዘጠኙ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ በመሆኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በልዩ ድምቀት ይከበራል ብለዋል።

ይኸውም አዲስ አበባ ከተማ የቅዱስ ሲኖዶስ ርዕሰ መንበር እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት በጃን ሜዳ ባሕረ ጥምቀት የሚከበረው በዓል እንደተጠበቀ ሆኖ በጠቅላላ በከተማዋ ውስጥ ከ78 ያላነሱ የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ሥፍራዎች ይገኛሉ ነው ያሉት።

በዚህም መሠረት በዓሉ በተቀናጀ መልኩ ለማስኬድ ሲባል በእያንዳንዱ ክ/ከተማ ላይ ግብረ ኃይል በማደራጀት እና ተጠሪነታቸውንም ለሃገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በማድረግ በሰፊው ዝግጅት ተደርጓል፣ በየባሕረ ጥምቀቱም በብዙህ ሺህ የሚቆጠሩ ምእመናን ይሳተፉበታል ብለዋል።

ሀገረ ስብከቱም በዓሉ በሰላም እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያካሄደውን ሰፊ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በሰላም አምላክ የተመሰረተን እና የተሰጠን ጸጋ ማስጠበቅ የእያንዳንዱ አማኝ ግዴታ ያሉት አቡነ ሄኖክ እንዲሁም የጥምቀት በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ መጠን ሰላምን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ድርሻ በእያንዳንዳችን ላይ እንዳለ በመገንዘብ ሐዋርያዊት ፣ ብሔራዊት እና ዓለምአቀፋዊት ለሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚመጥን መልኩ በዓሉን ማክበር ያስፈልጋል ብለዋል።
ስለሆነም ይህንን በዓል በምናከብርበት ወቅት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን ሰላም በመንከባከብ እና በመተግበር ፍፁም ክርስቲያናዊ በሆነ ሥነ ምግባር እና አካሄድ በዓላችንን ልናከብር ይገባናል ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ጥር 08 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *