የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጋሞ ዞን፣ በቆላ ሻራ ቀበሌ ውስጥ የደረሰውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ በሚመለከት ከነሐሴ 22 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በአካባቢው በመገኘት ያደረገውን ምርመራ ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም የሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለመረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ምርመራውን ለማከናወን ከተጎጂዎች፣ ከዐይን ምስክሮች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ በፖሊስ ጣቢያ ተይዘው ከነበሩ ተጠርጣሪዎች፣ በተለያዩ መዋቅሮች ሥር ከሚገኙ የመንግሥት የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የትምህርት መዋቅር ኃላፊዎች ጋር ቃለ መጠይቆችን እና የቡድን ውይይቶችን ጭምር እንዳደረገ ገልጻል፡፡
ለምርመራው አግባብነት ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን ከሆስፒታል፣ ከከተማ አስተዳደር ተቋማት እና ከተጎጂዎች አሰባስቧል፣ እንዲሁም ከክስተቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቦታዎች ላይ ኮሚሽኑ በአካል ምልከታ ማድረጉን ነው ያስታወቀው፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ተጠያቂነትን ከማረጋገጥና የተጎዱትን ከመካስ በተጨማሪም ለዚህና ተመሳሳይ ግጭቶች ምክንያት የሆነው የአካባቢ አስተዳደር መዋቅር ጥያቄና ውዝግብ ነዋሪዎችን ተዓማኒ በሆነ መንገድ ባሳተፈ ሰላማዊ ውይይት አፋጣኝ መፍትሔ ይሻል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሦስት ያልታጠቁ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ የፈጸሙና ያሰፈጸሙ፤ በቁጥጥር ሥር በዋሉ ሰዎች ላይ ድብደባ የፈጸሙ እንዲሁም በሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ የመንግሥት የጸጥታ አባላት እና ሌሎችም ሰዎች ላይ አስፈላጊ የሆነውን የተሟላ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ጠይቋል፡፡
እንዲሁም ለሟቾች ቤተሰቦች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና ንብረታቸው ለወደመባቸው ሰዎች፣ ለደረሰባቸው ጉዳት ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፈል ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
በሔኖክ ወ/ገብርኤል
ጥር 09 ቀን 2016 ዓ.ም
