የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደኅንንት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ የደኅንነት ስጋት የምትደቅን አገር ሳትሆን ለሶማሊያ ጥበቃ ለማድረግ ወታደሮቿን ማሰማራቷን አስታውሰዋል።
ሁለቱ አገራት ከጉርብትናቸው በላይ አንድ ቋንቋ እና ባሕል የሚጋሩ ሕዝቦች እንዷላቸው አስታውሰው፤ “እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ በችግሯ ጊዜ ለሶማሊያ ድጋፍ ሳያደርጉ የቆዩ አንዳንድ ኃይሎች እራሳቸውን እውነተኛ ወዳጅ አድርገው ለማሳየት እየሞከሩ ነው” ብለዋል።
በግልጽ ስም ባልጠሩበት ሁኔታም “የሚያነሳሳቸው ከሶማሊያ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ያላቸው ጥላቻ እንደሆነ ግልጽ ነው” ብለዋል አምባሳደር ሬድዋን በኤክስ ገጻቸው።
አምባሳደር ሬደዋን በቀጠናው ያሉ አንዳንድ ኃይሎች አጀንዳ በአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መፍጠር ነው ካሉ በኋላ ኢትዮጵያ ውጥረት ከሚያባብሱ መግለጫዎች እና ንግግሮች ይልቅ ቀጣይነት ያለው ንግግር ጠቃሚ ነው ብላ ታምናለች ብለዋል።
“አሁን እያየን ያነው አጉል ጀብደኝነት ውጥረትን የሚያባብስ” እንዲሁም “ለአድርባይ የውጭ አካላት ጥቅም የሚመች” እንደሆነም አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት በውድ ልጆቿ ደም እና ላብ በመገበር አስመስክራለች” ሲሉም አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በተመለከተ ባለፈው ሳምንት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት የልማት ድርጅት (ኢጋድ) እና የአረብ ሊግ በተናጠል ስብሰባ ማድረጋቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ያልተሳታፈችበት የኢጋድ ስብሰባ አገራቱ ውጥረቱን በማርገብ ንግግር እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያቀርብ፣ የአረብ ሊግ ደግሞ ኢትዮጵያን በማውገዝ ለሶማሊያ ድጋፉን ገልጿል።
ጥር 13 ቀን 2016 ዓ.ም
