የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለመስራት ካቀዳቸዉ 54 የዲዛይን ፕሮጀክቶች ዉስጥ 21 ያህሉን በጸጥታ ችግር መተግበር እንዳልቻለ አስታወቀ

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን የ 2016 ዓ.ም የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል።

አስተዳደሩ በወራቱ ለመከወን ካከቀዳቸዉ 54 የዲዛይን ፕሮጀክቶች ዉስጥ 21 ያህሉን በጸጥታ ችግር መተግበር እንዳልቻለ ዋና ዳይሬክተሩ ለቋሚ ኮሚቴዉ ተናግረዋል።

በዚህም በስድስቱ ወራት የነበረዉ የዲዛይን ስራዎች አፈጻጸም 57 በመቶ ሲሆን ይህም ዝቅተኛ እንዲሆን እንዳደረገበት ጣቢያችን ሰምቷል። በተጨማሪም በዉጭ አማካሪ ድርጅት ለተሰራ ስራ ክፍያ የዉጭ ምንዛሪ በመዘግየቱ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች መኖራቸዉንም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

በተለያዩ ምክኒያቶችም 84 ፕሮጀክቶች መቋረጣቸዉ እና ሙሉ በሙሉ የኮንትራት ዉላቸዉ መሰረዙም ተነግሯል።

የግብዓት እጥረት ፣ የወሰን ማስከበር ችግር እና የተጋነነ የካሳ ተመን ተቋሙ በወራቱ ካጋጠሙት ችግሮች ዉስጥ ችግር ሆነዉ መቀጠላቸውን አስረድተዋል።

ሌላዉ አስተዳደሩ በመንገዶች ጥገና እና ግንባታ በወራቱ የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን በኢትዮጵያ 169 ሺህ 450 ኪ.ሜ መድረሱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን መናገራቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል::

ልኡል ወልዴ
ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *