ኢትዮጵያ ከሱማሊላንድ የምታገኘዉን ወደብ ከወታደራዊ ዓላማ ይልቅ ለንግድ መጠቀሙ ይበጃታል ተባለ።

ከሱማሌላንድ ጋር የተደረገዉ ስምምነት ዕዉን መሆን ከቻለ፣ ከባህር ሀይል ይልቅ ለቢዝነስ መጠቀሙ የተሻለዉ አማራጭ ነዉ ስለመባሉ ሰምተናል።

ጣብያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም አቶ ዳዊት ተሻለ ከተባሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አቶ ዳዊት እንደሚሉት፣ የሚገኙ አማራጮችን ለንግድ ዓላማ መዋል አለባቸዉ፣በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የንግድ ትስስር የተጠናከረ ሲሆን ግጭቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ፡፡

ለጅቡቲ ወደብ በቀን 3ሚሊዮን ዶላር በዓመት እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ድርስ ወጪ ይደረጋል፣ ክፍያዉም በዉጪ ምንዛሬ የሚደረግ በመሆኑ ይህንን እየከፈሉ እስከ መቼ መቀጠል ይቻላል ሲሉም ይጠይቃሉ።

ለዚህም አማራጮችን መመልከት አስፈላጊ ነዉ የሚሉት ባለሙያው፤ በተለይም ከሱማሊላንዱ በተጨማሪ ሌሎች ወደቦችንም በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።

ከሱማሊለንድ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀዉ ወደብ ጠቀሜታዉ በረጅም ግዜ የሚገኝ ነዉ ይላሉ።

ምክንያቱ ደግሞ ወደቡን ማልማት መሰረተ ልማቶች ማሟላት ይኖርበታል ያሉ ሲሆን፣ ለዚህ መፍትሄዉ የለሙ ወደቦችን ለማግኘት መጣር እንደሆነ ገልፀዋል።

ከሰሞኑ የሱማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ከሀገሪቱ ቴልቭዥን ጣብያ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ “ለኢትዮጵያ የሚሰጠዉ የወደብ ቦታ ለወታደራዉ አገልግሎት ብቻ የሚዉል ነዉ” ማለታቸዉ ይታወሳል።

በአቤል ደጀኔ

ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *