በዝቋላ ስለተገደሉት የሃይማኖት አባቶች የኦሮሚያ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አገልጋይ የሆኑት አራት የገዳሙ አባቶች በአሽባሪዉ ኦነግ ሸኔ መገደላቸዉ ታውቋል፡፡

በነዚህ የሃይማኖት አባቶች ላይ የተፈፀመዉ ግድያ የወረዳዉን ማህበረሰብ ያስደነገጠና በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን ለሰላምና ፀጥታና ለፖሊስ የደረሰዉን ጥቆማ ተከትሎ አሽባሪዉን የማደን እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብሏል::

የወረዳዉ ማህበረሰብም እንደ ከዚህ በፊቱ በየደረጃዉ ከሚገኘዉ የመንግሥት መዋቅር ጋር ሆኖ ይህን አሸባሪ እንድያጋልጥ በድጋሚ እንጠይቃለን ሲል ገልጻል፡፡

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመሆን በአሸባሪ ኃይሉ ላይ በሚወሰደዉ እርምጃ የሚገኘዉን ዉጤት ለህዝብ በቀጣይነት እንደሚያሳዉቅ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትናንት ባወጣቸው መግለጫ፤ “በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም እራሱን ኦነግ ሸኔ ብሎ በሚጠራው ቡድን የገዳሙን መጋቢ ጨምሮ አራት አባቶችን መግደሉን ገዳሙ አስታውቋል” ስትል መግለጫ ማውጣቷ የሚታወስ ነው፡፡

ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ታጣቂዎቹ ሦስት አባቶችን አግተው ወደ በረሃ ከወሰዱ በኋላ የታገቱትን ለማስለቀቅ ገዳሙ ጥረት በሚያርግበት ወቅት የካቲት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተጨማሪ አባቶችን በመያዝ ግድያ መፈጸሙን ቤተ ክርስርቲያኗ አስታውቃለች።

አባ ኪዳነማርያም ገብረሰንበት የተባሉት አባት ቆስለው በገዳሙ እንደሚገኙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትናትን ባወጣችው መግለጫ፤ የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ገዳማዊያኑንና ገዳሙን የመታደግ ሥራ እንዲሠሩ ጠየቀች።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *