በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ ያልተቻለዉ በኢትዮጵያ ጥፋት ነዉ ስትል ግብጽ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርጋለች፡፡
የግብጽን ትችት የገልፍ አገራት የደገፉት ሲሆን፤ በአባይ ወንዝ ዙሪያ የግብጽ እና የሱዳንን መብት የሚጋፋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴን እንደማይቀበሉትም ነዉ የገለጹት፡፡
የግብጽ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹክሪ በገልፍ አገራት የትብብር ስብሰባ ላይ ስለ ህዳሴ ግድብ አንስተዉ ለገልፍ አገራት የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል ነዉ የተባለዉ፡፡
የአገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ኢትዮጵያ የምታንጸባርቀዉ አቋም መልካም ጉርብትናን የሚሸረሽር እንዲሁም ግብጽ በንግግሩ ላይ ተሳታፊ እንዳትሆን የሚያደርጋት ነዉ ሲሉ ሚኒስትሩ መግለጻቸዉን አስታዉቋል፡፡
ባለፈዉ ታህሳስ ወር ላይ ግብጽ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የተደረገዉ ድርድር ያለ ስምምነት መቋጨቱን አስታዉቃ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ-ግብጽ እና ሱዳን መካከል የተደረገዉ ንግግር መነሻዉ ሶስቱ አገራት የተስማሙበት እና በአራት ወራት ጊዜ ዉስጥ ግድቡ የሚሞላበት እና ስራ በሚጀምርበት የጋራ መግባቢያ ላይ የተመረኮዘ ነበር፡፡
በወቅቱ የግብጽ የመስኖ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ በአዲስ አበባ ተደርጎ የነበረዉ ስብሰባ ኢትዮጵያ ሶስቱንም አገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የትኛዉንም ዓይነት የቴክኒካል አልያም ህጋዊ መንገዶችን ለመጠቀም አሻፈረኝ በማለቷ ምንም ዓይነት ዉጤት ማግኘት አልተቻለም ሲል ማስታወቁ የሚታወስ ነዉ፡፡
በእሁዱ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የገልፍ አገራት ትብብር ምክርቤት ዋና ጸሀፊ የግብጽ እና የሱዳን የዉሃ ደህንነት ለአረብ አገራት ደህንነትም ጭምር ወሳኝ ጉዳይ ነዉ ያሉ ሲሆን፤ የአባይን ወንዝ ከመጠቀምም ሁለቱን አገራት የሚገድብ ማንኛዉንም ዓይነት እንቅስቃሴ የገልፍ አገራት በፍጹም የሚቀበሉት አይሆንም ነዉ ያሉት፡፡
የገልፍ አገራት ትብብር ምክርቤት ያስተላለፈዉ መልዕክት የኢትዮጵያን የአስተዳደር ጉዳዮች የሚተች ፖለቲካዊ መልዕክት ያዘለ ንግግር ነዉ የተባለ ሲሆን፤ አገራቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶች ስላሏቸዉም ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ ተብሏል፡፡
በእስከዳር ግርማ
የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም
