የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (ኢአማ) በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከታተል እና ለመመዝገብ የሚያስችል sojethiopia.org የተሰኘ ድረ-ገፅ ወይም ፖርታል አዘጋጅቶ በስራ ላይ አውሏል።
ደህረ ገፁ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ እና ባህል ድርጅት (UNESCO) ድጋፍ በኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር ተዘጋጅቶ በስራ ላይ መዋሉን በተቋማቱ በዛሬው እለት በተሰጠው መግለጫ ተገልፃል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ የዋለው ይህ ፖርታል በመጀመሪያው ምዕራፍ በሶስት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ ፣ ኦሮምኛ እና እንግሊዝኛ ተዘጋጅቷል፡፡

ድረ-ገፁ በጋዜጠኞች እና በብዙሃን መገናኛ ተቋማት ላይ የሚደርሱ እንደግድያ ፤ ማስፈራሪያ እና ዛቻ ፤ የመስሪያ ቦታ ማሸግ እና ፈቃድ ክልከላ ፤ ፆታዊ ጥቃት ፤ እስር ፤ እገታ ፤በማህበራዊ ሚድያ እና በሌሎችም መንገዶች የሚደረጉ ማንቋሸሽ ፣ ዘለፋ ፣ ስም ማጥፋት ፣ እና የመሳሰሉትን በመመዝገብ ፣ በማጣራት እና ለቀጣይ ውትወታ ስራዎች ግብአት በመሰብሰብ መገናኛ ብዙሃን ነፃነታቸው ተጠብቆ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ግንባታ ሂደት ላይ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
sojethiopia.org ጋዜጠኞች ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት የሚደርስባቸውን ማዋከብ እና የመሳሰሉት ክስተቶች ሲያጋጥም ከመመዝገብ እና ከመከታተል በተጨማሪ በተለየ ሁኔታ ፤ ሴት ጋዜጠኞች በስራ ቦታቸዉም ሆነ በጋዜጠኝነት ጉዞአቸው ላይ የሚደርስባቸውን ፆታዊ ጥቃቶችን ሚስጥራዊነቱ በተጠበ ጠበቀ መንገድ የሚመዘግብ እና የመፍትሄ ሒደቶችን ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የሚያመቻችበት ማዕቀፍ ነው ተብሏል፡፡
በየውልሰው ገዝሙ
መጋቢት 05 ቀን 2016 ዓ.ም
