በሀገሪቱ የሚወጡ ፓሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሰዎች ምቹ አይደለም ተባለ።

በሀገሪቱ የሚወጡ ፓሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ሰዎች ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠረ አይደለም ሲል ፍቅር የኢትዮጵያ አይምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር አስታውቋል።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች በጤና ፣በማህበራዊ ጉዳይ እና በትምህርት ላይ በሚወጡ ፓሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ላይ ተሳቢ አለመደረጋቸው እንደሚፈለገው ድጋፍ አጊኝተን መንቀሳቀስ እንዳንችል አድርጎናል ሲል ማህበሩ ለአኢትዮ ኤፍኤም አስታውቋል።

የፍቅር ኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር ዋና ኘሬዝዳንት ምህረት ንጉሴ እንዳስታወቁት የአይምሮ እድገት ውስንነት በገጠማቸው ሰዎች ላይ ከቤተሰብ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ እጥረቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል።

በዚህ የጤና እክል ላይ በሀገራችን ባለው የግንዛቤ እጥረት ምክንያትም የአዕምሮ እድገት ውስንነት አጋጥሞ ስራ የተቀጠረ እና እራሱን ችሎ መኖር የቻለ ሰው ማግኘት አለመቻላቸውንም አንስተዋል።

ማህበሩ ላለፉት 28 አመታት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች እና ወላጆቻቸው በተለያዮ በማህበራዊ በኢኮኖሚያዊ እና በማንኛውም ማህበረሰብ ነክ ጉዳዬች ላይ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎችን በሰፊው ሲሰራ እንደቆየ ተናግረዋል።

የማህበሩ ኘሬዝዳንት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆቻችንን ስለመብታቸው እንዲያውቁ እና እንዲጠይቁ የማድረግ ስራዎችን አሁን በሰፊው እየሰራንበት እንገኛለንም ብለዋል።

በሁለት ቦታዎች በ22 እና ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ የሙያ ማሰልጠኛ በማቋቋም የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች በማሰልጠን እንደሚያስመርቁም ተናግረዋል።

ሆኖም ማዕከሉ ብዙ የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ቢያስፈልገውም በቂ ድጋፍ እያገኘን አይደለም ሲሉ ኘሬዝዳንቷ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ5 ሚሊዮን በላይ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች መኖራቸውንም ገልፀዋል።

የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች መስራት ፣እራሳቸውን ችለው መኖር እና መማር አይችሉም የሚለው የማህበረሰቡ አስተሳሰብ መቅረፍ እንደሚገባም የማህበሩ ኘሬዝዳት ምህረት ንጉሴ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል።

በሐመረ ፍሬው

መጋቢት 09 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *