ለ 14 አዳዲስ የፊንቴክ ኩባንያዎች ፍቃድ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

ከዚህ በፊት ከነበሩት 11 የፊንቴክ ኩባንያዎች በተጨማሪ ለአዳዲስ የፊንቴክ ኩባንያዎች ፍቃድ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን የባንኩ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል።

ከ2019 በፊት የፊንቴክ ኩባንያዎች እንዲሰሩ ፍቃድ አልነበረም ያሉት አቶ ማሞ፤ ፍቃድ ከተሰጠ በኋላ ግን ፍላጎቱ ከፍ እያለ መጥቷል ብለዋል።

በሚቀጥሉት አመታት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ላይ መሠረታዊ ለውጥ ይመጣልም ነው ያሉት።

እንደ ብሄራዊ ባንክ ደግሞ ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የክፍያ ስትራቴጂ እና አዋጅ አለን ያሉ ሲሆን ፤በቅርቡ ደግሞ አዲስ ወጥ የሆነ የባንክ የፋይናንስ ህግ እናወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።

የባንኩን ዘርፍ ለውጭው ክፍት በምናደርግበት ጊዜ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት መሠረታዊ ለውጥ ይኖረዋል ብለዋል ዋና ገዢው።

ቁጠባን ወደ ኢንቨስትመንት በመውሰድ የኢኮኖሚውን ምርታማነትን ከፍ የሚያደርገው ይሆናልም ነው ያሉት።

ይህም ሁኔታውን ዲሞክራሲያዊ ያደርገዋል ያሉት አቶ ማሞ ፤ማንም ሰው ያለማስያዣ ብድሮችን ማግኘት እንዲችል የሚያደርግ አሰራር ይኖራል ብለዋል።
የተለያዩ ተቋማት ወደ ዘርፉ ሲገቡ አሁን ያለው ክፍያን ብቻ መሠረት ያደረገ አሰራር ወጥቶ የተሟላ የፋይናንስ አገልግሎት ወደመስጠት ይሸጋገራል ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ማሞ ከሰሞኑ በንግድ ባንክ ሲስተም ላይ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ከፍተኛ ምርመራ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልፀው ከሳምንት በኋላ ሪፖርቱ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *