በኢትዮጵያ ለተማሪዎች ዉጤት መቀነስ ምክንያቱ ‹‹ከፍተኛ የሙቀት መጠን ነዉ›› ሲል የዓለም ባንክ ገለጸ፡፡

የዓለም ባንክ አደረግኩት ባለዉ ጥናት በኢትዮጵያ ለተማሪዎች ዉጤት መቀነስ ምክንያቱ ከፍተኛ የሙቀት መጠን መጨመር ነዉ ብሏል፡፡

ከፈረንጆቹ 2003-2019 በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና የወሰዱ ወደ 2.5 ሚሊየን የሚጠጉ ተማሪዎችን ዳታ ሰብስቦ ያገኘዉ ዉጤት መሆኑን ነዉ ይፋ ያደረገዉ፡፡

በትምህርት ዓመቱ ለከፍተኛ ሙቀት የተዳረጉ በተለይ ደግሞ በፈተና ወቅት ከባድ ሙቀት የሚያገኛቸዉ ተማሪዎች ፤ቀዝቃዛ አየር ባለባቸዉ ስፍራዎች ከሚማሩ ተማሪዎች ጋር ሲወዳደር ዉጤታቸዉ በእጅጉ ቀንሶ ተገኝቷል ነዉ ያለዉ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ተጽዕኖ በተለይ በሰብ-ሰሃራ አፍሪካ አገራት ላይ የበረታ ነዉ የተባለ ሲሆን፤ የአየር ንብረት ለዉጡን ለመቋቋም የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በስፋት አለመኖራቸዉ ሁኔታዉን እንደሚያባብሰዉም ነዉ የተገለጸዉ፡፡

የጥናቱ መሰረታዊ ግኝት የሆነዉ በትምህርት ዘመኑ ከፍተኛ ሙቀት የሚስተናገድባቸዉ ቀናት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸዉ እንዲቀሩ የሚያደርግ መሆኑን ነዉ፡፡

ይህም በኮሌጅ መግቢያ ፈተናዎች ላይ ወደ 2.28 በመቶ ዝቅ ያለ ዉጤት እንዲመዘገብ እንደሚያደርግ ነዉ፡፡

በጥናቱ ይፋ እንደሆነዉ ግልጽ የሆነ ምክንያት ባይቀመጥለትም ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በሙቀት መጨመሩ ምክንያት የፈተና ዉጤታቸዉ ዝቅ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ከወንዶች ጋር ሲነጻጸሩም ሴቶች በተሻለ መልኩ በትምህርት ገበታቸዉ ላይ የሚገኙ እና ለትምህርታቸዉም ከፍተኛ ቦታ ያላቸዉ ሆነዉ ተገኝተዋል፡፡

አሁን ላይ በተለያዩ የአለማችን አገራት ለተማሪዎች ዉጤት መቀነስ የሙቀት መጨመር ምክንያት መሆኑን ማስረጃ አለን ሲሉ በዓለም ባንክ የሪሰርቸሮች ግሩፕ ዋና ተመራማሪ ፓትሪክ ቤህረር ተናግረዋል፡፡

ፓትሪክ ጨምረዉም ከፍተኛ ሙቀት ከተማሪዎቹ በተጨማሪ በመምህራን የስራ እንቅስቃሴ ላይም የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል ነዉ ያሉት፡፡

ፖሊሲ አዉጪዎች ይህንን ጉዳይ በደንብ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ያሉት ተመራማሪዉ ፤በመማሪያ ክፍሎች ዉስጥ ያለዉን የሙቀት መጠን በማስተካከል ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ ስፍራን መፍጠር አለባቸዉ ብለዋል፡፡

የተሻለዉ አማራጭ እንደየአከባቢዉ የሚለያይ ቢሆንም ግን አንድ ነገር ግልጽ ነዉ ሲሉ የሚጨምሩት ተመራማሪዉ ፤ይህም ተማሪዎች ለከፍተኛ ሙቀት ያልተጋለጡ አከባቢዎች ላይ እጅግ በተሻለ ሁኔታ መማር እንደሚችሉ ነዉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በ2022 ዘ ጋርዲያን ይዞት በወጣዉ አንድ ጽሁፍ ከፍተኛ የሙቀት መጨመር በጥራት እንዳናስብ በማድረግ ፣ የማሰላሰል እና የማመዛዘን ችሎታችን ላይ ተጽዕኖ ስለሚኖረዉ ስህተት የመስራት ዕድላችንን ከፍ ያደርገዋል ሲል አስታዉቆ ነበር፡፡

በእስከዳር ግርማ

መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *