ከባድ የአዕምሮ ህመም (ስኪዞፈሪኒያ) ምንድን ነው?
ስኪዞፈሪኒያ የአማርኛ ፍቺ ባይኖረውም በዋናነት ከባድ የሆነ የአስተሳሰብ፣ የሀሳብ መዛባት መሆኑን በዘርፉ ባለሞያዎች አቻ ፍቺ ይሰጠዋል፡፡
ስኪዞፈሪኒያ ከባድ የሚባል የአእምሮ ህመም መሆኑ ይነገራል፡፡
ህመሙ ወጣቶችን የሚያጠቃ ሲሆን፤ አልፎ አልፎም ከ20 ዓመት በታች ያሉ ሰዎችን ያጠቃል ተብሏል፡፡ በዚህ ህመም የሚሰቃዩ ሰዎች የህክምና ክትትል ካደረጉ ከህመሙ የሚድኑበት ሁኔታ መኖሩ ተመላክቷል፡፡
ከ360 በላይ የአእምሮ ህመሞች መኖራቸውን የነገሩን የአእምሮ ሀኪም የሆኑት ዶክተር እስጢፋኖስ እንዳላማው፤ ከእውነታው ዓለም ማፈንገጥ (ሳይኮሲስ) አንዱ ነው ብለዋል፡፡ እውነታን በተዛነፈ መልኩ መረዳት እና የሌለ ወይም ያልተፈጠረ ነገርን እንደተፈጠረ ማሰብ ማለት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከሳይኮሲስ የአእምሮ ህመም ውስጥ አንዱ ስኪዞፈርኒያ ነው ብለውናል፡፡ የዶፓሚን ስርዓት መዛባት በዋናነት ተጠቃሽ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
መነሻ ምክንያት፤
• በቤተሰብ ይህ ህመም ከነበረ
• አደንዛዣ እጾችን መጠቀም በተለይም ካናቢስ በ6 እጥፍ ተጋላጭ ያደርጋል
• ስነ ልቦናዊ አና ማህበራዊ ጉዳዮች ህመሙን አባባሽ ናቸው ተብሏል፡፡
በህመሙ የሚሰቃዩ ሰዎች ላይ የሚስተዋሉ ምልክቶች
• ምክንያት በሌለው ጉዳይ ላይ መጠራጠር እና መጨነቅ
• ሌሎችን ሊያጋራ የማይችሉ ጉዳዮች ላይ እምነትን የማሳደር ሁኔታ ሊስተዋልባቸው እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
• ያለሆኑ ነገሮችን እንደሆኑ እና የተከናወኑ አድርጎ ማሰብ
• በነባራዊ ዓለም ላይ የማሆኑ ነገሮችን እንደሚሆኑ ማሰብ
• የተለየ ጸጋ እንዳለ ማሰብ
• እራስን ለአደጋ ማጋለጥ
• ለሌሎች የማይታይ፣ የማይሰማን ማየት፣ መስማት እና ማሽተት
• በንግግር መሃል ከሀሳብ መውጣት እንዲሁም ከማህበራዊ ህይወት እራስን ማግለል ይስተዋላል ተብሏል፡፡
ህክምናው፤
የሚስተዋሉ ምልክቶች እስከ 6 ወራት መቆየት እንዳለባቸው የገለጹ ባለሞያው፤ በ6 ወራት ውስጥ ለ አንድ ወር ያህል በጽኑ የሚታመሙ ይሆናል ብለዋል፡፡
ህክምናው በወራቶች ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ በቅድሚያ ምልክቶችን በማጥፋት እና በአንቲ ሳይኮቲክ መድኃኒት የተዛባውን የዶፓሚን ስርዓት ማስተካከል እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ስኪዞፈሪኒያ ከባድ የአይምሮ ህመም በመሆኑ የሰዎችን አስተሳሰብ ፣ ስሜት እና ባህሪ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽእኖ እንደሚያሳድር ተነግሯል፡፡
ህመሙን የሚያባብሱ እና እንዲያገረሽ የሚያደርጉ ጉዳዮች
• የስከዞፈርኒያን መድሃኒት በድንገት ማቆም
• አደንዛዥ እጾችን መጠቀም
• አካላዊ ህመሞችን ሳይታከሙ ሲቀሩ ለህመሙ ተጋላጭ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ስለ ስኪዞፈሪኒያ የአእምሮ ህመም ምንነት ፣ በታማሚ ላይ የሚስተዋሉ ምልክቶች እና ህመሙ ላለባቸው ሰዎች ምን አይነት እንክብካቤ መስጠት እንደሚቻል ለህብረተሰቡ ማስተማር እና ግንዛቤን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
ሚያዝያ 03 ቀን 2016 ዓ.ም
