የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት 230 ቢሊየን 398 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።የሁለተኛ ቀን ጉባኤውን እያካሄደ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በዛሬው ውሎ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት አንዱ ነው።
ረቂቅ በጀቱን በዝርዝር ያቀረቡት የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን፣ የታክስ አፈፃጸም በጎ አዝማሚያዎችን ታሳቢ በማድረግ የከተማ አስተዳደሩ የ2017 በጀት 230.39 ቢሊየን ብር እንዲሆን መደረጉን አብራርተዋል።የምክር ቤቱ አባላትም የቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን ያቀረቡ ሲሆን ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችም ምላሾች ተሰጥተዋል።
ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ከ2010 እና በ2011 እስከ 30 ቢሊየን ብር የነበረው ግብር አሰባሰብ ከዘንድሮው የገቢ አሰባሰብ አንፃር ስናየው እድገት ቢያሳይም ከተማዋ ልታመነጭ ከሚገባው አንፃር ብዙ መሥራት የሚጠበቅ በመሆኑ ግብርን በሐቀኝነት የመክፈል ባህልን ማዳበር ይገባል ብለዋል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሐምሌ10 ቀን 2016 ዓ.ም
