የአውሮፓ ኅብረት የ‹ሸንገን ቪዛ› ለማግኘት በአገሪቱ ፍርድ ቤቶች አመልክተው፣ መኖር አትችሉም ተብለው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተወሰነባቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው በሚል፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዝርዝራቸው ከቀረበ ዜጎች መካከል፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሌላ አገር ዜጎች መሆናቸውን ገልጧል።
ኅብረቱ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአውሮፓ ኅብረት በተለይም ‹‹ሸንገን ቪዛ›› ውስጥ በሚገኙ አገሮች ጥገኝነት የጠየቁ ኢትዮጵያውያን፣ ጉዳያቸው የመኖሪያ ፈቃድ የማያሰጥ ሆኖ ሲገኝ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ታይቶ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው የሚባሉትን ኢትዮጵያ እንድትወስድ ጥያቄ ማቅረቡን፣ ነገር ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አፋጣኝ ምላሽ ባለመገኘቱ ለኢትዮጵያውያን የሚደረገውን የቪዛ አሰጣጥ ሒደት ለማጥበቅ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
በወቅቱም የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ አማካይነት በሰጠው ምላሽ፣ የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚሰጠውን ቪዛ አስመልክቶ የወሰነውን ውሳኔ ካልቀየረ፣ መንግሥት ተመጣጣኝ ውሳኔ እንደሚወስድ ማስታወቁ አይዘነጋም።
ቃል አቀባዩ ጉዳዩን በተመለከተ ሰሞኑን እንደገለጹት፣ የአውሮፓ ኅብረት ካሳለፈው ውሳኔ ጋር የሚመጣጠን ሲባል ግዴታ የቪዛ ዕቀባ ወይም የአሰጣጥ ሒደቱን ማጥበቅ ማለት አይደለም።
አምባሳደር ነብዩ ‹‹ኢትዮጵያውያኑን የመመለሱን ሥራ ቀደም ሲልም አላቋረጥምን፡፡ ነገር ግን እርግጥ ነው የማጣራት ሒደቱ የራሱ የሆነ ጊዜ ፈጅቶ ነበር፤›› ብለዋል።
‹‹አውሮፓ ውስጥ በስደተኝነት አመልክተው ጥገኝነት ጠይቀውና አጠቃላይ ሒደቱ አልቆ በፍርድ ቤት እዚያ መኖር አትችሉም ተብሎ ውሳኔ የተሰጠባቸው፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የኤርትራ፣ የጂቡቲ፣ የሶማሊያና የሱዳን ዜጎች እንደሚገኙ የታወቀ ነው፤›› ብለዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ከተጠቀሱት አገሮች ጋር ካላት የሕዝብ ለሕዝብ የቋንቋና የባህል መወራረስ ጋር ተያይዞ፣ እነዚህ ሰዎች በእርግጥም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ማጣራት ስለነበረብን፣ ይህን የሚያጣራ ልዑክ ቡድን እዚያ ሄዶ እነዚህን የማጣራት ሥራ ሠርቶ፣ በተገኘው ውጤት ከቀረቡልን ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሌላ አገሮች ዜጎች ነበሩ፤›› ሲሉም አስረድተዋል።
ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
