ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል 3ሺህ5መቶ ለሚሆኑ ህፃናት ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠቱን የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አደይ አባተ ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ለአካል ጉዳተኛ ልጆች ነፃ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።
ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ በአጥንት ችግር እና በሌሎች አካል ጉዳት በሚያስከትሉ ችግሮች ውስጥ ለሚገኙ ልጆች ነፃ የቀዶ ህክምና ይሰጣል።
ዋና ስራ አስኪያጇ አደይ አባተ እንደገለፁት ሆስፒታሉ ስራ ከጀመረ ወደ 16 ዓመታት እንደሆነው በማንሳት፤ በሆስፒታሉ የሚሰጥ የትኛውም አገልግሎት ሙሉለሙሉ ከክፍያ ነፃ መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎቱን የሚፈልጉ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እንዲሁም የሚሰጠው አገልግሎት ከታካሚዎች ቁጥር ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ሆስፒታሉን የማስፋፋት ስራ መጀመሩንም ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለትም አዲስ የክሊኒካል ህንፃ ይፋዊ የግንባታ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል።
የማስፋፊያ ስራው በ2 ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ በዕቅድ የተያዘ ሲሆን ፤ ለግንባታው ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ዋና ስራ አስኪያጇ አንስተዋል።
ሆስፒታሉ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ1መቶ 18 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካል ጉዳተኛ ልጆች የተለያዩ የህክምና አገልግሎትን የሰጠ ሲሆን፤ ከ33 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከመላ አገሪቱ የመጡ ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ያገኙ ናቸው።
አሁን ላይ ከ3ሺህ በላይ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ልጆች በጥበቃ ላይ መሆናቸውን የሚያነሱት ዋና ስራ አስኪያጇ፤ በሚፈለገው ልክ አገልግሎቱን እንዳይሰጡ የፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም መኖሩን ይገልፃሉ።
የሚደረጉት የቀዶ ህክምናዎች በጣም ውስብስብ እና ረጅም ሰዐትን የሚፈጁ መሆናቸውን የገለፁት አደይ፤ አሁን ላይ በዘመቻ መልክ በሳምንት ለ5 ህፃናት የቀዶ ህክምናው እንደሚሰጥ አንስተዋል።
የሆስፒታሉ ማስፋፊያ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ አሁን ላይ በአጠቃላይ ከ3ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የተሰጠውን የቀዶ ህክምና አገልግሎት በዕጥፍ በማሳደግ 6 ሺህ ለሚሆኑ ህፃናት አገልግሎቱን ለመስጠት መታቀዱን ገልፀዋል።
በእስከዳር ግርማ
ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም
