በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ከ890 ሄክታር በላይ ሰብልን መጉዳቱ ተሰምቷል፡፡
የወረባቦ ወረዳ የኮሚኒኬሽን ሀላፊ አቶ ከድር ሰይድ ለ ኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በወረዳው ባሉ 4 ቀበሌዎች የጣለው ከባድ ዝናብ በንፋስ፣ በበረዶና በጎርፍ ምክንያት በሰብል ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።
በአራቱም ቀበሌዎች ባጋጠመው ከባድ ዝናብ በሰብሎች ላይ ያደረሰው የጉዳት መጠን እንደ ሰብሉ አይነትና እንደ ቀበሌው የሚለያይ ቢሆንም በሁሉም አካባቢዎች ላይ ከ75 እስከ 95.5 በመቶ የሰብል ምርቶቹ መውደማቸውን ገልፀውልናል፡፡
አቶ ከድር ገበሬዎቹ ማሽላቸው በአንድ ጀንበር ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ ከጥቅም ውጭ ሆኖባቸዋል ያሉ ሲሆን በአጠቃላይ የጉዳት መጠኑን በገንዘብ ለማወቅ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ነግረውናል።
በወረዳዋ የሚገኙ ገበሬዎች በዓመት በአማካኝ እስከ 15 ኩንታል ማሽላ እንደሚያመርቱና ይህንንም ሰብል ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ከጥቅም ውጭ እንዳደረገባቸው አቶ ከድር ገልፀዋል።
ልኡል ወልዴ
ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም
