በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የነዳጅ ማደያዎች ላይ በቂ የሆነ የነዳጅ አቅርቦት ቢኖርም የተሽከርካሪ ሰልፎች ግን ሊቀንሱ አለመቻላቸዉን ሰምተናል፡፡
በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት በቀለች ኩማ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤ በቂ አቅርቦት ባለበት ረጃጅም ሰልፎች መኖራቸዉ ለምንድነዉ የሚለዉን ለማጣራት የባለስልጣኑ እንዲሁም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የቁጥጥር ባለሙያዎች ምልከታ ማድረጋቸዉን ገልጸዋል፡፡
በሸገር ከተማ አስተዳደርና በመዲናዋ አጠቃላይ 1መቶ20 የነዳጅ ማደያዎች መኖራቸዉን ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ 1መቶ 14 የሚሆኑት ላይ ምልከታ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በምልከታዉ የተገኙ ዉጤቶች እንደሚያሳዩት የናፍጣ እና የሌሎች የነዳጅ አይነቶች ሳይሆን ቤንዚን ላይ ችግር መኖሩን ነዉ ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ይህም ከአቅርቦት አንጻር ሳይሆን ከአጠቃቀም የተነሳ መሆኑን ነግረዉናል፡፡
አብዛኛዎቹ ማደያዎች በብዛት የናፍጣ እንጂ የቤንዚን ማሽኖች እንደሌሏቸዉ እና ይህም ለመቅዳት ረጅም ሰዓትን የሚወስድ በመሆኑ ሰልፎች መኖራቸዉን ገልጸዋል፡፡
በቴሌብር መጠቀም አለመቻል እና ጥሬ ገንዘብ ይዞ በመምጣት ለመክፈል ረጅም ሰዓት መዉሰድ እንዲሁ ሌላዉ የታየ ችግር መሆኑንም ዳይሬክተሯ ነግረዉናል፡፡
መዲናዋ 42 በመቶ የነዳጅ አቅርቦት ድርሻ እንዳላት ያነሱት ወ/ሮ በቀለች ፤ በቀን 1.4 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ወደ ከተማዋ ይገባል ነዉ ያሉት፡፡
ምናልባት በአዲስ ዓመት እና በአረፋ በዓላት ወቅት በሹፌሮች አለመገኘት እና ጅቡቲ ላይ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ክፍተት በመኖሩ ምክንያት ምናልባት ለ3ት ቀናት ያህል ትንሽ ችግር ሊኖር ይችላል እንጂ ይህን ያህል የጎላ ክፍተት አልነበረም ብለዉናል፡፡
በመጨረሻም እንደ መፍትሄ የነዳጅ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ ማድረግ፣ የባለስልጣኑ ባለሙያዎች በየነዳጅ ማደያዎቹ ተገኝተዉ በፍጥነት አገልግሎቱ እንዲሰጥ ማድረግ እንዲሁም በየማደያዎቹ ነዳጅ በበቂ ሁኔታ መኖሩን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ወ/ሮ በቀለች ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
በእስከዳር ግርማ
መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም
