የኢትዮጵያ መድሃኒትና የህክምና መገልገያዎች አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፍ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶሌ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ፤ በዉጪ ምንዛሪ ዕጥረት ምክንያት ከዚህ በፊት 8 በመቶ የነበረዉ የመድሃኒት አቅርቦት ወደ 36 በመቶ ከፍ ማለቱን ነግረዉናል፡፡
ከዚህ በፊት የዉጪ ምንዛሪ ዕጥረት መኖሩን የሚያነሱት ዶ/ር ዳንኤል፤ ወደ አገር ዉስጥ የጥሬ ዕቃ ለማስገባት አስቸጋሪ በመሆኑ ለመንግስት የሚቀርበዉ የመድሃኒት መጠን ያነሰ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ከዛ በኋላ መንግስት 55 በመቶ የዉጪ ምንዛሪ ድጋፍ መፍቀዱን ተከትሎ ከዉጪ ጥሬ ዕቃ በስፋት በመግባቱ የሚቀርበዉ የመድሃኒት መጠን ወደ 36 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ፍቃድ ከጠየቁ እና ወደ ስራ ከገቡ 14 መድሃኒት አምራች ኢንዱስትሪዎች ዉስጥ 6ቱ ምርታቸውን ወደ ውጭ ሃገራት በመላክ ላይ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በፊት ከባንኮችም ዶላር አይገኝም ከዉጪም ገዝቶ መጠቀም አይቻልም ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤በቅርቡ የተደረገዉ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ገበያ መር መሆኑ ለዘርፉ የሚጠቅም መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጲያ በየአመቱ ለመድሀኒት እና ለህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዢ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደምታደርግ ከዚህ ቀደም መገለጹ ይታወሳል፡፡
በእስከዳር ግርማ
መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም
