ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጰያ የተደረገዉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዉን ተከትሎ የኩላሊት እጥበት የሚሰጡ ተቋማት የህክምና ግብአቶችን አሁን ባለዉ የዉጭ ምንዛሬ በማስመጣታቸዉ ለታማሚወች የሚሰጡትን የኩላሊት እጥበት ዋጋ መጨመሩን የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሰለሞን አሰፋ ለጣቢያችን ተናግረዋል።
ታካሚዎች በሳምንት ዉስጥ ከአስራ ሁለት እስከ አስራ አራት ሺ ብር ለህክምና ያወጣሉ ያሉት አቶ ሰለሞን ዲያልሲስ የሚያደርጉ ታካሚዎች የአቅም ዉስንነት እየታየባቸዉ በመሆኑ ህይወታቸዉ ማጣታቸዉን ይገልፃሉ ።
በየቀኑ ቁጥሩን መጥቀስ የሚያዳግት ዲያሌሲስ የሚያደረግ ሰዉ ነዉ የሚመጣዉ ያሉት አቶ ሰለሞን ለአንድ እጥበት ከ 3 እስከ 4 ሺ ብር እየተጠየቀ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህን ተከትሎ ህሙማኑ የኩላሊት እጥበት መጠኑን ከሶስት ወደ አንድ ለማዉረድ እየተገደዱ ነዉ ተብሏል።
የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ማህበር አሁን ላይ የዲያሌሲስ ሴንተሮችን በየሆስፒታሉ ለመክፈት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል
ሊዲያ ደስአለኝ
ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም
