በፍሎሪዳ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “የአሜሪካ ሕዝብ 47ኛው ፕሬዝደንት አድርጎ ስለመረጠኝ ላመሰግን እወዳለሁ” ያሉት ዶናልድ ትራምፕ “ለሁሉም ዜጋ” ለመታገል ቃል ገብተዋል።
“ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ታላቅ ድል ነው፤ አሜሪካን እንደገና ታላቅ ለማድረግ ያስችለናል” ሲሉም የምርጫ ዘመቻ መፈክራቸውን በመጠቀም ተናግረዋል።
ትራምፕ ድላቸውን ለደጋፊዎቻቸው በተናገሩበት የፍሎሪዳ መድረክ “አገራችን እንድትድን እንረዳታለን” ብለዋል።
በድንበሮች ያሉ ጉዳዮችን እልባት እንደሚሰጡ ቃል ገብተው ፓርቲያቸው እና እሳቸው ታሪክ የሰሩት በምክንያት ነው ብለዋል።
ትራምፕ በዚህ የድል ንግግራቸው ይህችን ዕለት “በህይወታችሁ ጠቃሚ የምትባል ዕለት አድርጋችሁ እንደምትቆጥሯት” ተስፋ አለኝ ብለዋል።
“አሜሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ስልጣን ሰጥታናለች” በማለት ፓርቲያቸው የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱን የበላይነት ከዲሞክራቶች በመውሰድ መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።
ይህንን ተከትሉም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኤማኑዌል ማክሮ የአሜሪካ 47ኛ ፕሬዝደንት ሆነው ለመመረጥ ለተቃረቡት ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም
