በኢትዮጵያ ከተመረቱ በኋላ የሚባክኑ ምርቶች መጠን ከፍተኛ መሆኑን ሰምተናል።
ከምንመገበው የምግብ መጠን 30 በመቶው እንደሚጣል እና ከአትክልትና ፍራፍሬ ደግሞ 50 በመቶው ለብክነት እንደሚጋለጥ የኢትዮጵያ ሥርዓተ ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ አስታውቋል።
በጅማ ዩኒቨርስቲ የሥርዓተ -ምግብ ፕሮፌሰር እና ከኔትዎርኩ መስራቾች አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ተፈራ በላቸው፤ ከመንዝ የመጣ ድንች ለምግብነት ሳይበቃ 70 በመቶው እንደሚጣል እና ከአርባምንጭ የሚመጣ የሙዝ ምርት ደግሞ 50 በመቶው እንደሚባክን በቅርቡ የተሰራ ጥናት ማመልከቱን ለጣቢያችን ተናግረዋል።
በምንም አይነት ቴክኖሎጂ ብናመርት የሚባክነውን ያህል መልሶ የማምረት አቅም የለንም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ማህበረሰቡ የአመጋገብ ዕውቀት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
ከ6 ዓመት በፊት የፀደቀው የምግብና ሥርዓተ -ምግብ ፖሊሲ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ የድህረ-ምርት ብክነት ቅነሳ ላይ እና የአመጋገብ እውቀትን ለማስፋት እየተሰራበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ስድስተኛው የኢትዮጵያ ሥርዓተ-ምግብ መሪዎች ኔትዎርክ አመታዊ ጉባኤውን ቅዳሜ ዕለት አካሂዷል።
የዚህኛው ዓመት ጉባኤ “የሥርዓተ-ምግብ አመራር በአየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር የሥርዓተ – ምግብ ትግበራ በኢትዮጵያ ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
እስከዳር ግርማ
ኀዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም
