በአዲስ አበባ ከተማ በጥቅምትና ህዳር ወር ብቻ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በተፈፀመ ስርቆት ከ1.6 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል።
ከዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ደቡብ ሪጅን አከባቢዎች በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በተፈፀመ ስርቆት ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የአገልግሎቱ የኮምኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ መላኩ ታየ ለጣቢያችን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን በየካ ክፍለ ከተማ ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትራንስፎርመርና የኃይል ስርቆት ተፈፅሟል ብለዋል።
በጉለሌ፣ ኮልፌ፣ አራዳ፣ ቂርቆስና ልደታ ክፍለ ከተሞች በተፈፀመ የኬብልና የሌሎች መሰረተ-ልማቶች ስርቆት ከ2 መቶ ሺህ ብር በላይ ኪሳራ መድረሱንም ነው ስራ አስፈፃሚው የነገሩን።
በተለያዩ ጊዜያት በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ በሚፈፀም ስርቆት ምክንያት ለዜጎች ይቀርብ የነበረው የኃይል አቅርቦት መቋረጡ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብለዉናል።
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም አቶ መላኩ ነግረውናል።
ሊዲያ ደሳለኝ
ኀዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም
