ተቋማቱ በመረጃ ነፃነት አዋጁ ለሕዝቡ የሚጠበቅባቸውን መረጃ እንዲያደርሱ ቢቀምጥም ሪፖርቱን እያቀረቡ አለመሆኑ ተገልፆል።
የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የሚቀርብለት የመረጃ ነፃነት ሪፖርት የዜጎች መረጃን የማግኘት መብት ግልጽነት እና ተጠያቂነት ለማምጣት እንደሆነ ይገልፃል ።
በኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የህግ ዝግጅት ክፍል ሀላፊ የሆኑት አቶ ተመስገን ኪዳኔ ተቋማቱ ላይ በተደረገ ግምገማ የመረጃ ነፃነት ሪፖርቶች አለመቅረባቸዉን ተመልክተናል ሲሉ ለኢትዩ ኤፍም ተናግረዋል።
መረጃዎች በተፈለገዉ ልክ ያለመላክ ክፍተት ተቋማቱ ላይ እንደሚታይ የሚገልፁት ሀላፊዉ ሆኖም አዋጁ የመንግሰት ተቋማት ሪፖርቱ እንዲቀርብ ግዴታ የሚጥል ነዉ ይላሉ።
የህዝብ ግንኙነት እና የመረጃ ክፍል ባለሙያዎች ላይ ስለ መረጃ ነፃነት ሪፖርቱ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰራ መሆኑን የተቋሙ የህዝብ ዝግጅት ክፍል ሀላፊዉ ይገልፃሉ።
ይህንን የመረጃ ነፃነት ሪፖርት በትክክል ለማስፈፀም እንዲቻል አዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ እንደተዘጋጀለት አቶ ተመስገን ለጣቢያችን ተናግረዋል ።
በተጨማሪም ተሻሽሎ በረቀቀዉ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ሪፖርቱን ማቅረብ ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ የግል ተቋማትን የሚጨምር እንደሆነ ተጠቅሷል።
ይህንን የተሻሻለ አዋጅ አፅድቆ ወደ ስራ በማስገባት የዜጎችን የመረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ እንዲቻል ምክር ቤቱ በትኩረት እንዲመለከተዉ ተጠይቋል።
ቁምነገር አየለ
ኀዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም
