“ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ሌላ፤ ኦሮሞነት ደግሞ ሌላ ነው፤ ኦሮሞነቴ ከኢትዮጵያዊነቴ ጋር ተጋጭተውብኝ አያውቁም” በሚለው ንግግራቸው የሚታወቁት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በማረፋቸው የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡
በሚችሉት ሁሉ ሀገራቸውንና አፍሪካን ያገለገሉ፣ በአቋማቸው ጽኑ፣ ሕዝቦችን ለማቀራረብ የተጉ፣ እውነት ነው ብለው ያመኑትን የትምና መቼም የሚናገሩ ነበሩ ብለዋል፡፡
እንዲህ ዓይነት ብርቱ ሽማግሌዎችን ማጣት ጉዳቱ ለሀገር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይቀበላት ሲሉም ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት ገልጸዋል፡፡
አቶ ቡልቻ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ቢርመጂ ወረዳ ከአባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ናሲሴ ሰርዳ በ1923 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ናቸው፡፡
በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የገንዘብ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር እንዲሁም የዓለም ባንክ የአፍሪካ ተወካይ በመሆን ሠርተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀጥረው በተለያዩ ሀገራት አገልግለዋል።
አቶ ቡልቻ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አዋሽ ባንክ ሽልማት አበርክተውላቸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርስነት የሚያዝ የልዩ ታሪካዊ ሁነቶች ማስታወሻ የወርቅ ሳንቲም የሸለማቸው ሲሆን፣ አዋሽ ባንክ ደግሞ የምስጋና የምስክር ወረቀት፣ ካባ እና የወርቅ ሜዳሊያ አበርክቶላቸዋል።
ታኀሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም
