ወጋገን ባንክ ወጋገን ኢ-ብር የተሰኘ የሞባይል ዋሌት አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡

ደንበኞች ወደ ባንክ ቅርንጫፍ መሄድ ሳይጠበቅባቸዉ በሞባይል ስልካቸዉ መተግበሪያ አማካኝነት የሞባይል ዋሌት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት መሆኑን አስታዉቋል፡፡

የወጋገን ኢ-ብር የሞባይል ዋሌት አገልግሎት ደንበኞች ካሉበት ሆነው በማንኛውም ጊዜ ገንዘብ ማስተላለፍ እና ክፍያ መፈፀም እንደሚያስችላቸው የባንኩ የኢንተርፕራይዝ ሰርቪስስ ም/ሥራ አስፈፃሚ አቶ የኋላሸት ዘውዱ ገልፀዋል፡፡

የሞባይል ዋሌት አገልግሎቱ የባንኩን ተደራሽነት ከማስፋት እና አገልግሎቶቹን የበለጠ አካታች ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅዎ እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል፡፡

የኢ-ብር ሞባይል ፋይናንሻል ሰርቪስስ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ በእውቀት ታፈረ፤በኢ-ብር ፕላትፎርም ከብር 2 ትሪሊየን በላይ ግብይቶች መፈፀማቸውን ገልፀው ኢ-ብር ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች አካታች ባደረገ መልኩ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ አስተዋፅኦ እንዳለዉ አንስተዋል፡፡

የወጋገን ኢ-ብር የሞባይል ዋሌት አገልግሎት ከፕሌይ ስቶር ወይም አፕ ስቶር የኢ-ብር መተግበሪያውን በማውረድ ወይም ወደ *602# በመደወል ደንበኞች በቅድሚያ ወጋገን ባንክን በመምረጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

በወጋገን ኢ-ብር ሞባይል ዋሌት አገልግሎት በመጠቀም ደንበኞች የሞባይል አየር ሰዓት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬት፣ የውሃ አገልግሎት ፣የትምህርት ቤት፣ የፈረስ ትራንስፖርትን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች ክፍያ መፈፀም እንደሚችሉ ታውቋል፡፡

የባንክ ሂሳብ የሌላቸው ግለሰቦችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡

በ16 ባለአክሲዮኖች በብር 60 ሚሊዮን የተፈረመ መነሻ ካፒታል እና በብር 30 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ወጋገን ባንክ፤ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉ ከብር 6 ቢሊዮን በላይ እንዲሁም ጠቅላላ ካፒታሉ ብር 11 ቢሊዮን በላይ መድረሱም ተገልጿል።

እስከዳር ግርማ

ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *