በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ የተፈጸመው የጥቅምት 7 – 2023 ጥቃት መከላከል ባለመቻላቸው የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዳልተወጡ የገለጹት ሌተናል ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ ለመከላከያ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፤ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት “የእስራኤልን ዜጎች የመጠበቅ ኃላፊነቱን አልተወጣም” ብለዋል።
“ይህንን ኃላፊነት ባለመወጣቴ በየቀኑ እና በየሰዓቱ አብሮኝ ያለ ሲሆን በቀሪው ህይወቴም አብሮኝ ይቀጥላል” ሲሉ አክለዋል፡፡
ምንም እንኳን የእስራኤል የጦርነት ግቦች “ሁሉም” አንዳልተሳኩ ያመኑት ጄኔራሉ ለሰራዊቱ “ጉልህ ስኬቶች” በተመዘገቡበት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 6 ሥራቸውን እንደሚለቁ ተናግረዋል።
“ጦሩ ሐማስን እና አመራሩን የበለጠ በማውደም ታጋቾቹ እንዲመለሱ ለማድረግ” እና በታጣቂ ቡድኖች ጥቃት የተፈናቀሉ እስራኤላውያን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በማድረግ ትግሉ ይቀጥላል ብለዋል።
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ የእስራኤል ጦር የደቡባዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ያሮን ፊንከልማን “ምዕራብ ኔጌቭን እና የሚወዷቸውን ጀግኖች ነዋሪዎቿን” የመጠበቅ ግዴታቸውን አልተወጣሁም በሚል ከኃላፊነት እንደሚነሱ አስታውቀዋል።
ከ15 ወራት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ከጋዛ የሚያዋስናትን አጥር ጥሰው በአካባቢዎቹ ባሉ የእስራኤል ማህበረሰቦች ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት የእስራኤል ወታደራዊ እና የስለላ ባለስልጣናት ብዙ ማስጠንቀቂያዎችን ባለመስማት ወይም ችላ በማለታቸው ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ታግተዋል።
የመከላከያ ሃይሉ በጋዛ የአየር እና የምድር ዘመቻ በመክፈት ምላሽ የሰጠ ሲሆን ከ47 ሺህ 100 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም
