ትራምፕ የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶችን መጠን ለመቀነስ በያዙት ዕቅድ ነው ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት።
አስተዳደራቸው በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ለፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች በላከው ኢሜይል ስራቸውን በገዛ ፈቃድ መልቀቅ ለሚፈልጉ እና በዚህ ፕሮግራም መካተት ለሚፈልጉ እስከ ጥር 29/ 2017 ዓ.ም ቀነ ጊዜ እንደተሰጣቸው አትቷል።
በተቀመጠው ቀነ ገደብ ወቅት ስራቸውን ለመልቀቅ ከተስማሙ የስምንት ወር ደመወዛቸውን እንደ የስንብት ፓኬጅ እንደሚያገኙ ከተላከው ኢሜይል መረዳት ይቻላል።
የትራምፕ አስተዳደር እስከ 10 በመቶ የሚደርሱት ወይም 200 ሺህ የሚሆኑት ሰራተኞች ይህንን ፓኬጅ እንደሚቀበሉ እንደሚጠብቅ የቢቢሲ አሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።
በአሜሪካ የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ሰራተኞች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን በላይ ይሆናል።
የትራምፕ ከፍተኛ ባለስልጣን ይህ እርምጃ መንግሥትን እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ያህል ለማዳን እንደሚያስችለው ለአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት በተጻፈው ኢሜይል ላይ በዚህ የሚስማሙ ሰራተኞች “መልቀቅ” በሚል ርዕስ ኢሜይላቸውን አርቅቀው እንዲመልሱ ተጠይቀዋል። የሚለቁ ሰራተኞች እስከ መጪው መስከረም ድረስ የሚሆን ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያገኙ ይሆናል።
ሆኖም የፖስታ ቤት ሰራተኞች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት እንዲሁም የተወሰኑ የብሔራዊ ደህንነት ሰራተኞች በዚህ ፓኬጅ እንዳልተካተቱ ኢሜይሉ አትቷል።
በስራቸው ላይ ለመቆየት የወሰኑ ሰዎች ለወደፊቱ ሊቀነሱ እንደሚችሉ የሰራተኞች አስተዳደር ጽህፈት ቤት የወጣው ይህ ኢሜይል አስጠንቅቋል።
ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም
