በ12ኛው ዙር 50 ድርጅቶች ይሳተፋሉ ምዝገባውም እስከ የካቲት 15 ይቁያል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅትና ሃያሰባት ማርኬቲንግና ብራንዲንግ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅትና ሃያሰባት ማርኬቲንግና ብራንዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት እና የሃያሰባት ማርኬቲንግና ብራንዲንግ አቶ አስቻለው ታምሩ ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅትና ሃያሰባት ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ በጋራ ለመስራት ከተስማሙባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የሚያከናውነውን የተለያዩ ተቋማትን የመመዘን ሂደትና ሥራ በተለያየ መልኩ ሃያሰባት ማርኬቲንግ እና ብራንዲንግ በሙያው ያግዛል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የጥራትና ልህቀት ጽንሰ ሐሳብን ለማስረጽና ጥራት የአገሪቱን ባሕል እንዲሆን ለማስቻል የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማስተዋወቅ እና ተደራሽ በማድረግ ያግዛል ብለዋል ።
በተጨማሪም በሁለቱም አካላት በኩል የሥልጠና አገልግሎት ፈልገው ለሚመጡ ድርጅቶች የሥልጠና አገልግሎት ፍላጎታቸውን ለማሟላት በእጃቸው ላይ የሚገኙ ባለሙያዎችን እና መሣሪያዎችን በማቀናጀት በጋራ አብረው እንደሚሰሩ ተገልጿል።
የሃያ ሰባት ማርኬቲንግና ብራንድንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ታምሩ፤የአገሪቱን ተወዳዳሪነት ለማሳደግና ጥራት በአገሪቱ ባህል እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም ከጥራትና ከልህቀት ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን ለተለያዩ ድርጅቶች በመስጠት ጥራት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት፤ ድርጅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የጥራት ሽልማት የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬውም ስምምነት የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች የሚሰጡትን አገልግሎት በተሻለ ጥራት እንዲሰጡ እና ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ ያስችላል ብለዋል።
አቶ ቴዎድሮስ የ12ኛ ዙር የጥራት ሽልማት ውድድር ምዝገባ መጀመራቸውንና ምዝገባው እስከ የካቲት 15 እንደሚቆይም ተናግረዋል።
በዘንድሮ አመት 50 ድርጅቶችን ብቻ ነው ምናወዳድረውም ብለዋል።
ልኡል ወልዴ
ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም
