የኦርጋኒክ ቡና ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በአለም ገበያ የግዢ መስፈርት አስገዳጅ ሆኗል።
ሆኖም ለዉጪ ገበያ የሚቀርብ ቡና ከኬሚካል ነፃ አበቃቀልን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ማቅረብ የሚያስገድድ ቢሆንም የላብራቶሪ ምርመራ ለማድረግ ከፍተኛ ዉጪ የሚያስወጣ ነዉ ተብሏል።
የዩኒየኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ዳዲ ከአዉሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ህግ በበለጠ እየተቸገረን ያለዉ ይህንን የማረጋገጫ ወረቀት ማግኘት ነዉ ሲሉ ከኢትዩ ኤፌም ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
አምስት መቶ ሺህ ገበሬዎች በዉስጡ የያዘዉ ዩኒየኑ የዚህን ማረጋገጫ ለማግኘት ከእያንዳንዱ ገበሬ ማሳ 5 በመቶ የቅጠል ናሙና ምርመራ ለማድረግ ወደ ደብብ አፍሪካ እና ጀርመን እየተላከ መሆኑ ተገልፆል።
አቶ ደጀኔ ምርመራዉ የሚጠይቀዉ የላብራቶሪ ዉጪ ስራዉን ከባድ እና ፈታኝ እያደረገዉ መሆኑን አንስተዋል።
አክለዉም የዩኒየኑን ወጪ ለማገዝ ከቡና ገዢዎች ጋር የወጪ መጋራት ( cost sharing) እንዲኖር ድርድሮች እየተደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ የቡና ገበሬዎች ዩኒየን እስካሁን ከካርበን ሽያጭ 1.7 ሚሊየን ዩሮ ማግኘት እንደቻለ አቶ ደጀኔ ተናግረዋል።
ይህም በወለጋ አካባቢ የተሞከረ ሲሆን መቶ ሺህ ሜትሪክ ቶን የተገኘበት ነዉ ተብሏል።
የካርበን ሽያጩ በምስራቅ እና ምእራብ ጉጂ ÷ ጅማ÷ ቡኖ በደሌ÷ እና ኢሊባቡር ላይ በዚህ አመት ተግባራዊ እንደሚደረግ ዩኒየኑ ለኢትዩ ኤፌም አስታዉቋል።
ቁምነገር አየለ
ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም
