የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ማቋቋምያ ሰነድ ጥር 2015 ዓ.ም ሲፀድቅ በተነሳው ሃሳብ መሰረት ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ በመምረጥ የአማካሪ ካውንስል ምክር ቤት ተመስርቷል፡፡
በምስረታ ካውንስሉ መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዜዳንት ጌታቸው ረዳ ፤ በክልሉ የሚገኙ የኢሮብ እና ኩናማ ብሄረሰቦች የተወከሉበት ካውንስሉ ዘግይቶም ቢሆንም መመስረቱ መልካም ሆኖ አቃፊ ፣ አሳታፊ እና የሃሳብ ብዙህነት የሚንሸራሸሩበት መድረክ መሆን ይገባዋል ብለዋል።
የካውንስሉን ምስረታ አስመለክተው ሃሳባቸውን ለኢትዮ ኤፍ ኤም የሰጡን የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚተ አባል አቶ ገ/ጊዮርጊስ ግደይ “የምክር ቤቱ ምስረታ ህጋዊ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ብለዋል”፡፡
አቶ ገ/ጊዮርጊስ “ሁሉም ነገር በህግ ሊገዛ ይገባል ይህ ካልሆነ ካውንስሉ ለትችት ክፍት እንዳይሆን ያሰጋኛል ያሉ ሲሆን አስፈላጊነቱ ባያጠያይቅም ህጋዊነቱ ግን በደንብ ሊፈተሸ ይገባል ብለዋል”፡፡
ጊዜዓዊ አስተዳደሩ ካውንስሉን ሲያቋቋም ህዝቡን ወክሎ ነው የፌደራል መንግሰትን ወክሎ ነው የሚለው ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የካውንስሉ እድሜ የጊዚያዊ አስተዳደሩ የቆይታ ጊዜ መሆኑ ፕሬዜዳንት ጌታቸው በምስረታው ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ገ/ ጊዮርጊስ ግደይ የቆይታ ጊዜውም ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው ያሉ ሲሆን ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ጋር በቀጥታ እድሜውን ማያያዝ ልክ አይደለም ጊዜአዊ አስተዳደሩ ቢወርድ እንኳን አማካሪ ካውንስሉ እንደሚቀጥል ማሰብ ይገባል ብለዋል፡፡
የካውንስሉ ምስረታ እና አላማ ለህዘቡ ጥሩ እና ብዙሃኑን የሚያስማማ መሆኑን የነገሩን ሲሆን ተጠሪነቱም ለህዝቡ መሆን እንዳለበትም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር አማካሪ ካውንስል ምክር ቤት ለመምራት ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢውን የመረጠ ሲሆን አቶ ሞገስ ታፈረን የምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ አድርጎ ሲመርጥ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑትን ዶ/ር ደጀን መዝገቦን ምክትል ሰብሳቢ ሆነው መመረጣቸውም ተዘግቧል፡፡
ለአለም አሰፋ
ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም
